Tuesday, July 9, 2013

ኑ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንስራ መ.ነህ 2:20

ስለ መድኃኔዓለም የበረከት ተካፋይ እንሁን

የላፍቶ ሌንቃ መድሐኔዓለም ቤተክርስቲያንን ከፍጻሜ ለማረስ የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎች ቀለም ለውስጥና ውጭ ግድግዳ,ጂብሰም ,ፐርሊል ,ሞራሌ,ሚስማር ,መጋረጃ ,ምንጣፍ ,መንበር ,የበረንዳ ግሪል,ጎረንዳዬ ,ደውል ,ጀሶ ,ዘኮሎ ባለ 10፤ኮላ፤ የመሬት ሸክላ(ቴራዞን) በረንዳ ዙሪያ ለማንጠፍ፤ በደንብ የተጠረበ ከድንጋይ የተሰራ ወለል ንጣፍ በቤ/ክ ዙሪያ፡፡ ለነፍሳችን ቤዛ የሚሆንልንን መንፈሳዊ ስራ በመስራት የአቅማችንን በማድረግ የተጀመረውን ህንጻ ቤተክርስቲያን ከፍጻሜ እናድርስው፡፡
ኑ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንስራ መ.ነህ 2:20…
ቅዱስ እንጦንስ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር Commercial Bank of Ethiopia, Bomb Tera Branch. Account no. 1000017080249 mobile +251911143653, +251911780816, +251910016008
ክብር ምስጋና ለመድሓኔአለም ይሁን፡ለፍፃሜው አድርሶ የበረከቱ ተካፋይ ለመሆን ያብቃን፡፡


LIKE >>>

 https://www.facebook.com/pages/ቅዱስ-እንጦንስ-መንፈሳዊ-የአገልግሎት-ማኅበር/473117159405402?ref=hl

Thursday, May 23, 2013

ኑ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንስራ መ.ነህ 2:20




የላፍቶ ሌንቃ መድሐኔዓለም ቤተክርስቲያንን ከፍጻሜ ለማረስ የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎች ኮርኒስ በፒ.ቪ.ሲ፣ ቀለም ለውስጥና ውጭ ግድግዳ,ጂብሰም ,ፐርሊል ,ሞራሌ,ሚስማር ,መጋረጃ ,ምንጣፍ ,መንበር ,የበረንዳ ግሪል,ጎረንዳዬ ,ደውል ,ጀሶ ,ዘኮሎ ባለ 10፤ኮላ፤ የመሬት ሸክላ(ቴራዞን) በረንዳ ዙሪያ ለማንጠፍ፤ በደንብ የተጠረበ ከድንጋይ የተሰራ ወለል ንጣፍ በቤ/ክ ዙሪያ፡፡ ለነፍሳችን ቤዛ የሚሆንልንን መንፈሳዊ ስራ በመስራት የአቅማችንን በማድረግ የተጀመረውን ህንጻ ቤተክርስቲያን ከፍጻሜ እናድርስው፡፡ ኑ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንስራ መ.ነህ 2:20… ቅዱስ እንጦንስ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር Commercial Bank of Ethiopia, Bomb Tera Branch. Account no. 1000017080249 mobile +251911143653, +251911780816, +251910016008 ክብር ምስጋና ለመድሓኔአለም ይሁን፡፡

ትንሣኤ ዘክርስቶስ


(ይህ ጽሑፍ ለ፪፼፪ ዓም ትንሣኤ በማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ላይ ወጥቶ የነበረ ነው።)

ጌታችን  አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድኅነተ ዓለምን በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወረደ÷ ይኸውም በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረትን ሊያስቀርልን ነው፡፡ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወረደ÷ ይኸውም በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ነፃነትን ይሰብክላቸው ዘንድ ነው፡፡ መለኮት፥ በተዋሕዶ፥ ከሥጋም ከነፍስም ጋር ነበረ፡፡ ለዚህ ነው፥ መቃብር ሥጋን ሊያስቀረው ያልቻለው፤ ሲኦልም ነፍስን ማስቀረት አልተቻለውም፡፡ ቅዱስ ዳዊት፡- « ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተዋትም» ያለው ይኽንን ታላቅ ምሥጢር በትንቢት ቃል ሲናገር ነው፡፡ መዝ ፲፭÷፲፡፡ ሐዋርያው  ቅዱስ ጴጥሮስም፡- «ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር (ወደ አብ÷ ወደ ራሱና ወደ መንፈስ ቅዱስ) እንዲያቀርበን፥ እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት (ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ተላልፎ በመሰጠት) ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ (በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ለየ)÷ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ÷ (ያን ሥጋ ነፍስ እንድተለየችው መለኰት አልተለየውም)÷ በእርሱም ደግሞ (መለኰት በተዋሐዳት ነፍስ) ሄዶ በወኅኒ ለነበሩት ነፍሳት ሰበከላቸው፤» ብሏል።

፩፥፩፦ ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት በመቃብር፤
ጌታችን በከርሰ መቃብር የቆየው ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ነው፡፡ «ሥጋዬ ደግሞ በተስፋ ታድራለች፤» የሚለው ቃለ ትንቢት የሚያረጋግጥልን ይኽንኑ ነው፡፡ መዝ ፲፭፥፱፡፡ ምሥጢራዊ ትርጉሙም «ወደ መቃብር የወረደ ሥጋዬ በተስፋ ትንሣኤ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በመቃብር አደረ፤» ማለት ነው፡፡ ተስፋ ትንሣኤውም በተዋሕዶ ከሥጋ ጋር ወደ መቃብር የወረደ መለኰት ነው፡፡ ነቢዩ ሆሴዕም፡- «ኑ÷ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና÷ (በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስን ጨምሮ የፈረደብን እርሱ ነው)÷ እርሱም ይፈውሰናል፤ (መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን አስወግዶ ከሞት ወደ ሕይወት ያሸጋግረናል)፤ እርሱ መትቶናል÷ እርሱም ይጠግነናል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፡፡» በማለት ትንሣኤ ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ሆሴ ፮÷፲፪፡፡ ይልቁንም ጌታችን ራሱ በመዋዕለ ሥጋዌው፡- ከሽማግሌዎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀመዛሙርቱ በግልጥ ነግሯቸዋል፡፡ ማቴ ፲፮÷፳፩፡፡ በገሊላም ሲመላለሱ፡- «ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው÷ ይገድሉትማል÷ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤» ብሏቸዋል፡፡ ማቴ ፲፯÷፳፡፡ ጻፎችና ፈሪሳውያንም ምልክት በጠየቁት ጊዜ፡- «ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል÷ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ፥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ÷ እንዲሁ የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡» ብሏቸዋል፡፡ ማቴ ፲፪፥፴፰-፵።

፩፥፪፦ ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት የሞላው እንዴት ነው?፤

ጌታ በከርሰ መቃብር የቆየው ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ነው፡፡ ይኽንንም ለመረዳት ዕብራውያን ዕለታትን እንዴት እንደሚቆጥሩ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እኛ በሀገራችን የሌሊቱን ሰዓት መቁጠር የምንጀምረው ከዋዜማው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ነው÷ የቀኑን ሰዓት መቁጠር የምንጀምረው ደግሞ ከማለዳው አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ የሌሊቱ ሰዓት የሚያ ልቀው ከማለዳው አሥራ ሁለት ሰዓት ሲሆን፥ የቀኑ ደግሞ ከምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ሲሆን ነው፡፡ የቀኑም የሌሊቱም ሰ ዓት ተደምሮ ሃያ አራት ሰዓት ይሆናል፡፡ ሁሉም ሰዓት ዕለቱን ይወክላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው እሑድ ዕለት ከሃያ አራቱ ሰዓ ት በአንዱ ቢወለድ እሑድ ተወለደ ይባላል÷ ቢሞትም እሑድ ሞተ ይባላል፡፡ ዕለቱ በሚጀምርበትም ሰዓት ሆነ፥ በሚያልቅ በት ሰዓት፥ ድርጊቱ ቢፈጸም ያ ሰዓት እንደ አንድ መዓልትና እንደ አንድ ሌሊት ይቆጠራል፡፡ አውሮፓውያን አንድ ብለው ሰዓት መቁጠር የሚጀምሩት በእኛ አቆጣጠር ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ነው፡፡ እስከ ሃያ አራት ይቆጥሩና በእኛ አቆጣጠር ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሲሆን ይጨርሳሉ፡፡ ሃያ አራት ሰዓት ሲሆን ዜሮ ይሉና እንደገና አንድ ብለው መቁጠር ይጀምራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ከሌሊት እስከ ሌሊት ይቆጥራሉ፡፡ አሜሪካውያን ደግሞ በእኛ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን አንድ ብለው ይጀምሩና በእኛ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ሲሆን አሥራ ሁለት ብለው ይጨርሳሉ፡፡ ከዚያም በእኛ አቆጣጠር ከቀኑ ሰባት ሰዓት እንደገና አንድ ብለው ይጀምሩና በእኛ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሲሆን አሥራ ሁለት ብለው ይጨርሳሉ፡፡
 ዕብራውያን ግን ዕለትን መቁጠር የሚጀምሩት ከዋዜማው ማለትም በአውሮፓውያን ከአሥራ ሰባት ሰዓት÷ በአሜሪካውያን ከአምስት ሰዓት (P.M.) ÷ በእኛ ደግሞ ከምሽቱ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ድረስ ሃያ አራት ሰዓት ቆጥረው አንድ ቀን ይላሉ፡፡ ከላይ እንደተገለጠው እያንዳንዱ ሰዓት የዕለቱን መዓልትና ሌሊት ይወክላል፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ከመስቀል ወርዶ የተቀበረው ዓርብ ቅዳሜ ከመግባቱ በፊት ነው፡፡ ዓርብ ዕለቱ የሚጀምረው ከዋዜማው ሐሙስ በእኛ አቆጣጠር ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታ የተቀበረው በዓርብ ሃያ አራት ሰዓት ክልል ውስጥ በመሆኑ እንደ አንድ መዓልትና ሌሊት ይቆጠራል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ዓርብ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ቀን አሥራ አንድ ሰዓት ያለው ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ቅዳሜ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ እሑድ ቀን አሥራ አንድ ሰዓት ያለው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የሰኞ ምሽት ይገባል፡፡ ጌታ የተነሣው በሦስተኛው ቀን እሑድ መንፈቀ ሌሊት ነው።
፩፥፫፦ እንዴት ተነሣ?

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ነው፡፡ ይህ ኃይልና ሥልጣን የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ ይኽንንም፡- «ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ (ሰውነቴን ከሞት አነሣት ዘንድ) አኖራለሁና (በፈቃዴ እሞታለሁና)፤ ስለዚህ አብ ይወደኛል፡፡ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ (ነፍሴን በፈቃዴ ከሥጋዬ ለይቼ በገነት÷ ሥጋዬንም በመቃብር አኖራቸዋለሁ እንጂ) ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ (ያለ እኔ ፈቃድ የሚፈጸም ምንም ነገር የለም)፡፡ ላኖራት (ነፍሴን በገነት÷ ሥጋዬን በመቃብር ላኖራቸው) ሥልጣን አለኝ፤ ደግሞም ላነሣት (ነፍሴን ከሥጋዬ አዋሕጄ ላነሣት) ሥልጣን አለኝ፡፡» በማለት አስቀድሞ ተናግሮታል፡፡ ዮሐ ፲÷፲፯-፲፰፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ፡- «ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት÷ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈ ተም፡፡» በማለት መናገሩ ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ እንደሚሞት የሚያጠይቅ ትንቢት ነበር፡፡ ኢሳ ፶፫፥፯፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ከዚህ የሚመሳሰል ቃል ተናግሯል፡፡ ፩ኛጴጥ ፪÷፳፴፡፡ በዚህ ዓይነት ነቢያትም ሐዋርያትም የተናገሩለት ኢየሱስ ክርስቶስ በኃይሉ በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጐ÷ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሥቷል፡፡ እርሱ የትንሣኤና የሕይወት ባለቤት ነውና፡፡ ዮሐ ፲፩÷፳፭፡፡
ይህ እንዲህ ከሆነ÷ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፡- «የሕይወትን ራስ ገደላችሁት፤» በማለት አይሁድን ከወቀሳቸው በኋላ፡- «እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፤» ለምን አለ? የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፡፡ ይኽንን ኃይለ ቃል በመያዝ «አብ አስነሣው እንጂ በራሱ አልተነሣም፤» የሚሉ አሉና፡፡ እነዚህም ትርጓሜውን ያልተረዱ ምሥጢሩን ያላስተዋሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ሐዋርያው «እግዚአብሔር አስነሣው፤» ያለው «እግዚአብሔር» የሚለው ስም የሦስቱም መጠሪያ እንጂ የአብ ብቻ አለመሆኑን ስለሚያውቅ ነው፡፡ ምክንያቱም፦ ወልድም እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል፡፡ ዮሐ ፩÷፩ ፣ የሐዋ ፳÷፳፰፡፡ መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል፡፡ ዮሐ ፩÷፪፡፡ ስለዚህ፦ ሥላሴ በፈቃድ አንድ በመሆናቸው፥ «አንዲት በሆነች በአብ በራሱና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና ሥልጣን ተነሣ፤ አንድም፦ ወደ መቃብር የወረደ ሥጋ፥ መለኰት የተዋሐደው ስለሆነ ተነሣ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በመሆኑ ተነሣ፤» ተብሎ ይተረጐማል፥ ይታመናል፡፡ ትንቢተ ነቢያትም የሚያረጋግጥልን ይኽንኑ ነው፡፡ «እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ÷ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው፤ ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፤» ይላል። መዝ ፸፯፥፷፭።
፩፥፬፦ ለምን በአዲስ መቃብር ተቀበረ?

በእስራኤል ባሕል፥ የአባቶቻቸው አፅም ካረፈበት መቃብር፥ የመቀበር ልማድ አላቸው፡፡ ዮሴፍ በግብፅ የእስራ ኤልን ልጆች፡- «እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ፤» ብሎ ያማላቸው፥ የአባቶቹ የአብርሃም እና የይስሐቅ የያዕቆብም አፅም ካረፈበት ለመቀበር ፈልጐ ነው፡፡ ዘፍ. ፶÷፳፭፡፡ በቤቴል የነበረውም ሽማግሌ ነቢ ይ፡- «በሞትሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ አጥንቶቼንም በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ፤» ብሏል ፡፡  ፩ኛነገ ፲፫÷፴፩፡፡ ጌታችን የተቀበረው እንደ እስራኤል ባሕል የቅዱሳን አፅም ካረፈበት ሳይሆን ማንም ካልተቀበረበት ከአዲስ መቃብር ነው፡፡ ይኸውም ዮሴፍ ለራሱ ያዘጋጀው ነው፡፡ «ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው÷ ከዓለት በወቀረ ው በአዲሱ መቃብርም አኖረው÷ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ፤» ይላል ማቴ ፳፯÷፶፱፡፡ ይህም የሆነው እርሱ ባወቀ በርሱ ጥበብ ነው፡፡ እንዲህም በማድረጉ አይሁድ ለትንሣኤው ምክንያት እንዳያበጁለት አድርጓቸዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን እንደተጻፈው፥ ከነቢዩ ከኤልሳዕ መቃብር ተቀብሮ የነበረው ሰው፥ የነቢዩ አጥንት በነካው ጊዜ፥ በተአምር ተነሥቷል። ፪ኛነገ ፲፫÷፳፡፡ እንግዲህ ጌታችንም፥ ከአንዱ ቅዱስ መቃብር ተቀብሮ ቢሆን ኖሮ፥ ሞትን ድል አድርጐ በሚነሣበት ጊዜ «በራሱ አልተነሣም፥ የቅዱሱ አፅም ነው ያስነሣው፤» ባሉት ነበር፡፡ ይኸንን ምክንያት ለማጥፋት ነው፥ በአዲስ መቃብር የተቀበረው።

፩፥፭፦ እንዴት በዝግ መቃበር ተነሣ?

ጌታችንን ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ገንዘው ከቀበሩት በኋላ፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተመልሰው፡- « ጌታ ሆይ÷ ያ ሰው (ክርስቶስ)፥ ገና በሕይወቱ ሳለ፥ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ፥ እንዳለ ትዝ አለን፡፡ እንግዲህ ደቀመዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም  ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ÷ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት፡፡ ጲላጦስም፡- ጠባቆች አሉአችሁ፥ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ፤» አላቸው፡፡ እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ፡፡» ማቴ ፳፯፥ ፷፫÷፷፮፡፡ በታላቅ ድንጋይ የተገጠመው መቃብር፥ ድንጋዩ እንደታተመ፥ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ተነሥቷል፡፡ ይኸውም፦ ምንም የማያግደው መለኰት በተዋሕዶ ከሥጋ ጋር በመቃብር ስለነበረ ነው፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረው፥ በተዋሕዶ፥ የቃል ገንዘብ ለሥጋ፥ የሥጋም ገንዘብ ለቃል በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ አይሁድ ብዙ ጊዜ በድንጋይ ቀጥቅጠው ሊገድሉት ሲፈልጉ፥ እያዩት ይሰወርባቸው ከእጃቸውም ይወጣ ነበር፡፡ በመካከላቸው አልፎ ሲወጣ አያዩትም ነበር፡፡ ዮሐ ፰÷፶፱፤ ፲፥፴፱፡፡ ይህም የሆነው፥ እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶ፥ መለኰት ሥጋን በመዋሐዱ ነው፡፡ ከትንሣኤው በኋላም ከአንዴም ሁለት ጊዜ ከተዘጋ ቤት በሩ ሳይከፈት የገባው ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ ፳÷፲፱፤ ፳፮፡፡ በልደቱም ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና እንደታተመች የተወለደው ለዚህ ነው፡፡ ኢሳ ፯÷፲፬፡፡ ማቴ ፩÷ ፳-፳፫ ፣ ሉቃ ፪÷፮-፯፡፡

፩፥፮፦ መቃብሩን ማን ከፈተው?

         ጌታችን የተነሣው መግነዝ ፍቱልኝ፥ መቃብሩን ክፈቱልኝ ሳይል ከሆነ፥ «መቃብሩን ማን ከፈተው? ለምንስ ተከ ፈተ?»  የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፤ በወንጌል እንደተጻፈው፥ የአይሁድ ሰንበት ቅዳሜ ካለፈ በኋላ፥ እሑድ በማለዳ፥ ፀሐይ ሲወጣ፥ መግደላዊት ማርያም÷ የያዕቆብም እናት ማርያም ሶሎሜም ሽቱ ሊቀቡት ወደ መቃብሩ መጥተው ነበር፡፡ ትልቁ ጭንቀታቸው «ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል?» የሚል ነበር÷ ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና፤ አሻቅበውም አይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደነበር ተመለከቱ፡፡ ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጐናጸፈ ጐልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ፡፡ በጐልማሳ አምሳል የተገለጠላቸው የጌታ መልአክ ነው፡፡ እርሱ ግን፡- «አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ አውቃለሁ፤ ተንሥቷል በዚህ የለም፡፡» አላቸው፡፡ ማር ፲፮÷፩-፮፡፡ ጌታችን በዝግ መቃብር ከተነሣ በኋላ ባዶ የነበረውን መቃብር የከፈተው ይህ የጌታ መልአክ ነው፡፡ የከፈተበትም ምክንያት በእምነት የመጡ እነዚህ ሴቶች ያልተነሣ መስሏቸው ዘወትር በመመላለስ እንዳይቸገሩ ነው፡፡ አንድም ትንሣኤውን እንዳይጠራጠሩ ነው፡፡ በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልም «በሰንበትም መጨረሻ የመጀመሪያው ቀን ሲነጋ፥ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ፡፡ እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ፡፡ መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፡፡ ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ፡፡ እንደ ሞቱም ሆኑ፡፡ መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው፥ እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና፤ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤» የሚል ተጽፏል፡፡ ማቴ ፳፰÷፩-፮፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በእርግጠኝነት ትንሣኤውን ያመኑት መልአኩ ወደ ከፈተው መቃብር ገብተው መግነዙን ካዩ በኋላ ነው። ዮሐ ፳፥፯።

፩፥፯፦ በኲረ ትንሣኤ፤

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለባሕርይ አባቱ፥ ለአብ ለእናቱ ለድንግል ማርያምም የበኵር ልጅ ነው፡፡ ዕብ ፩÷፮፣ ሉቃ ፪÷፯፡፡ ለበጎ ነገርም ሁሉ በኵር በመሆኑ የትንሣኤያችንም በኵር እርሱ ነው፡፡ «አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኵራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል፡፡ ሞት በሰው (በቀዳማዊ አዳም) በኵል ስለመጣ፥ ትንሣኤ ሙታን በሰው (በተዋሕዶ ሰው በመሆኑ ዳግማዊ አዳም በተባለ በክርስቶስ) በኩል ሆኗልና፡፡ ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኵራት ነው፤» ይላል፡፡ ፩ኛቆሮ ፲፭÷፳-፳፫፡፡ በተጨማሪም፡- «በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥሯልና፥ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፡፡ (ከፍጥረታት በፊት የነበረ÷ የፍጥረታት አለቃ÷ የፈጠረውን ፍጥረት የሚገዛ ነው)፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሯል ፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፤ (ለዘመኑ ጥንት የሌለው ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት በህልውና የነበረ ነው)፤ ሁሉም በእርሱ ተጋጥሟል፡፡ እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርሰቲያን ራስ ነው፤ እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው፡፡» የሚል አለ፡፡ ቈላ ፩÷፲፮-፲፰፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም፡- «ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም÷ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት÷ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን፤» ብሏል። ራእ ፩፥፭።
 በብሉይ ኪዳን እነ ኤልያስ÷ እነ ኤልሳዕ ሙት አስነሥተዋል፡፡ ፩ኛነገ ፲፯፥፳፪ ፣ ፪ኛነገ ፬÷፴፪-፴፰፡፡ በአዲስ ኪዳንም ራሱ ባለቤቱ የመኰንኑን ልጅ ÷ የመበለቲቱን ልጅ÷ አልዓዛርንም ከሞት አንሥቷቸዋል፡፡ ማቴ ፱÷፳፭፣ ሉቃ ፯÷፲፭ ፣ ዮሐ ፲፩÷፵፬፡፡ ነፍሱን በመስቀል ላይ በፈቃዱ አሳልፎ በሰጠም ጊዜ አያሌ ሙታን ከእግረ መስቀሉ ተነሥተዋል፡፡ ማቴ ፳፯÷፶፫፡፡ እነዚህ ሁሉ በኵረ ትንሣኤ አልተባሉም፡፡ ምክንያቱም፦ አንደኛ፥ በራሳቸው ኃይል የተነሡ አይደሉም፡፡ ሁለተኛ፥ ለተወሰነ ጊዜ ከኖሩ በኋላ ተመልሰው ሞተው ትንሣኤ ዘጉባኤን የሚጠብቁ ሆነዋል፡፡ ሦስተኛ፥ ፍጡራን ናቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የባሕርይ አምላክ በመሆኑ በራሱ ኃይልና ሥልጣን ተነሥቷል፡፡ ዳግመኛም አይሞትም፡፡ ይኽንንም፡- «ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደፊት እንዳይሞት፥ ሞትም ወደፊት እንዳይገዛው እናውቃለንና ÷ መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቷልና፡፡» በማለት ሐዋርያው ገልጦታል፡፡ ሮሜ ፮÷፱፡፡ ጌታችንም፡- «ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፤» ብሏል። ራእ ፩፥፲፰።

፩፥፰፦ ከትንሣኤው በኋላ ለምን ተመገበ?

ጌታችን በተዘጋ ቤት ገብቶ ለደቀ መዛሙርቱ በተገለጠ ጊዜ፥ መንፈስ የሚያዩ መስሏቸው ኅሊናቸው ደንግጦ÷ ልባቸውም ፈርቶ ነበር፡፡ እርሱም፡- «ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት÷ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና፥ እኔን ዳስሳችሁ እዩ፤» ካላቸው በኋላ እጆቹንና እግሮቹን አሳይቷቸዋል። እነርሱም ከደስታ የተነሣ ገና ስላላመኑ ሲደነቁ ሳሉ፡- «በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን?» አላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ ከማር ወለላም ሰጡት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በላ፥ ይላል። ሉቃ ፳፬÷፴፮ -፵፫። ለሦስተኛ ጊዜ በጥብርያዶስ በተገለጠላቸውም ጊዜ አብሯቸው ተመግቧል፡፡ ዮሐ ፳፩÷፱-፲፬። ይኽንንም ያደረገው ከትንሣኤ በኋላ መብላት መጠጣት ኖሮ አይደለም፡፡ አለማመናቸውን ለመርዳት ነው፡፡ ደቀመዛሙርቱ በተዋሐደው ሥጋ ለመነሣቱ እርግጠኞች እንዲሆኑ ነው፡፡ ከወንጌሉ እንደምንረዳው ደቀመዛሙርቱ ይበልጥ እርግጠኞች የሆኑት ስላዩት ሳይሆን፥ ያቀረቡለትን በመብላቱና በመጠጣቱ ነውና፡፡
፩፥፱፦ ለምን አትንኪኝ አላት?

መግደላዊት ማርያም ገና ሰማይና ምድሩ ሳይላቀቅ፥ በማለዳ፥ ሽቱ ልትቀባው ከመቃብሩ አጠገብ ተገኝታ ነበር። እንደደረሰችም ድንጋዩ ከመቃብሩ አፍ ተፈንቅሎ አየች። ይህች ሴት በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ ከባለቤቱ ብትሰማም፥ « እንደተናገረ ተነሥቶ ነው፤» ብላ አላመነችም። ላለማመኗም ምክንያት የሆነው፥ «እኛ ተኝተን ሳለን ደቀመዛሙርቱ በሌሊት ሰረቁት፤» የሚለው የጭፍሮች ወሬ ነው። ጭፍሮቹ እውነትን በሐሰት ለውጠው ይኽንን ያወሩት፥ በገንዘብ ተደልለው ነው፡፡ ማቴ ፳፰÷፲፩-፲፭፡፡ ለዚህ ነው ወደ ደቀመዛሙርቱ ሄዳ፡- «ጌታን ከመቃብር ወስደውታል፥ ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም፤» ያለቻቸው፡፡ ዮሐ ፳÷፪፡፡ ከመቃብሩ ራስጌና ግርጌ ሁለት መላእክት ተገልጠውላት፡- «አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ?» ባሏት ጊዜም፥ «ጌታዬን ወስደውታል፥ ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም፤» ብላቸዋለች፡፡ ዮሐ ፳÷፲፫፡፡ በመጨረሻም ጌታ ራሱ ተገልጦላት፡- «አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ?» ሲላት አላወቀችውም፡፡ ለዚህ ነው፥ አትክልት ጠባቂ መስሏት፡- «ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደሆንህ፥ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ፥ እኔም ወስጄ ሽቱ እንድቀባው፤» ያለችው፡፡ ዮሐ. ፳÷፲፭፡፡ በዚህን ጊዜ፥ «ማርያም»፥ ብሎ በስሟ ቢጠራት በድምፁ አወቀችውና «ረቡኒ ( መምሕር ሆይ)» አለችው፡፡ መልኩን አይታ፥ ድምፁን ሰምታ÷ ትንሣኤውን አረጋግጣ፥ «አምላኬ» አላላችውም፡፡ ስለዚህ «ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ አትንኪኝ፥ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ (ወደ ደቀመዛሙርቴ) ሄደሽ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ÷ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አርጋለሁ ብሏል፥ ብለሽ ንገሪያቸው፤» አላት፡፡ እንዲህም ማለቱ የእርሱ የእግዚአብሔር ልጅ መባልና የእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች መባል ፍጹም የተለያየ በመሆኑ ነው፡፡ እርሱ፥ «አባቴ» ቢል የባሕርይ ልጅ በመሆኑ ነው፡፡ እነርሱ ግን የጸጋ ልጆች ናቸው፡፡ እርሱ፥ «አምላኬ» ቢል ስለተዋሐደው ሥጋ ነው፡፡ የተዋሐደው የፈጠረውን ሥጋ ነውና ፡፡ እነርሱ ግን «አምላካችሁ» ቢባሉ ፍጡራን ስለሆኑ ነው፡፡ በዚህም እርሱ ፈጣሪ እነርሱ ፍጡራን መሆናቸውን አስረግጦ ተናግሯል፡፡ ቶማስን ግን፡- «ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው ፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን፤» ብሎታል፡፡ ዮሐ ፳፥፳፯ ፡፡ ምክንያቱም አይቶ፥ ዳስሶ፥ «ጌታዬ አምላኬም» ብሎ የሚያምን ነውና፡፡ አንድም ሥጋውንና ደሙን ለመዳሰስ÷ ለመፈተት፥ የተጠራ የተመረጠም ካህን ነውና፡፡

፩፥፲፦ ተስፋ ትንሣኤ፤

በብሉይ ኪዳን ዘመን ሁሉም በአዳም ኃጢአት ምክንያት እየተኰነኑ በሞተ ነፍስ ተይዘው ወደ ሲኦል ይወርዱ ነበር ። ፩ኛ ቆሮ ፲፭ ÷፳፪፡፡ «ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ( እስከ ክርስቶስ) ድረስ ሞት ነገሠ፤» የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ሮሜ ፭÷፲፬፡፡ ከዚህ የተነሣ እነ አብርሃም እንኳ ሳይቀሩ የወረዱት ወደ ሲኦል ነው፡፡ እነ ኢሳይያስ፡- «ጽድቃችንም ሁሉ እንደመርገም ጨርቅ ነው፤» ያሉት ለዚህ ነው፡፡ ኢሳ ፷፬ ÷፮፡፡ እነ ኤርምያስም፡- «ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም፥ ስንዴን ዘሩ እሾህንም አጨዱ፡፡» ብለዋል፡፡ ኤር ፲፪÷፲፫። በዚህ ምክንያት የብሉይ ኪዳን፥ ዘመን ዘመነ ፍዳ÷ ዘመነ ኵነ ÷ ዘመነ ጽልመት ተብሏል፡፡ በዚህ ዘመን እነ ቅዱስ ዳዊት፡- «አንሥእ ኃይለከ÷ ወነዓ አድኅነነ፤ ኃይልህን አንሣ÷ እኛንም ለማዳን ና ፤ (በሥጋ ተገልጸህ÷ ሰው ሁነህ አድነን)፤» እያሉ ወልድን ተማጽነዋል፡፡ መዝ 79÷ 2 ፡፡ «ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ፤ ብርሃንህንና እውነትህን ላክልን፤ (ብርሃን ወልድን÷ እውነት መንፈስ ቅዱስን ላክልን) ፤ እነርሱ ይምሩን÷ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ÷ (ወደ ገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት) ይውሰዱን  »፤ እያሉም አብን ተማጽነዋል፡፡ መዝ ፵÷፫፡፡ ይህም የሚያመለክተው በዚያ በጨለማ ዘመን ሆነው ተስፋቸው የክርስቶስ ትንሣኤ እንደነበረ ነው፡፡ በሞት አጠገብ ሕይወት÷ በመቃብር አጠገብ ትንሣኤ እንዳለ ተስፋ እንዲያደርጉ የሚያደርጋቸው የክርስቶስ ትንሣኤ ነውና፡፡ ያንጊዜ ከሲኦል እንደሚወጡ፥ የተዘጋች ገነትም እንደምትከፈትላቸው ያውቃሉና፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ የአዳም ልጆች በጠቅላላ ትንሣኤ ዘጉባኤን በተስፋ እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ተስፋ ሃይማኖት እንዲይዙ÷ ምግባር እንዲሠሩ አጽንቷቸዋል፡፡ ምድራዊውን እንዲንቁ፥ ሰማያዊውን እንዲናፍቁ አድርጓቸዋል፡፡ « ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን፡፡» ይላል፡፡ ፪ኛ ጴጥ ፫÷፲፫፡፡ ቅዱሳን በሃይማኖት አይተዋታል፡፡ «አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ÷ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና÷ ባሕርም ወደፊት የለም፡፡ ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ፡፡» ይላል፡፡ ራእ ፳፩÷፫፡፡ እግዚአብሔርም፡- «እነሆ÷ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፥ የቀደሙትም አይታሰቡም÷ ወደ ልብም አይገቡም፡፡ ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ፥ ለዘላለምም ሐሴት አድርጉ፤ እነሆ÷ ኢየሩሳሌምን ለሐሴት÷ ሕዝቧንም ለደስታ እፈጥራለሁና፡፡» ብሏል፡፡ ኢሳ ፷፭፥፲፯።

፩፥፲፩፦ ሙታን እንዴት ይነሣሉ?


           እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው የሚያንቀላፋና የሚነቃ አድርጐ ፈጥሮታል፡፡ ማንቀላፋቱ የሞት፥ መንቃቱ ደግሞ የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ አቤል ከሞተ በኋላ በደሙ መናገሩም የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ ፬÷፲፡፡ የሄኖክም ከዓይነ ሞት ተሰውሮ በእግዚአብሔር መወሰድ የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ ፭÷፳፬፡፡ ፍጥረታት በጠቅላላም ትንሣኤን የሚሰብኩ ናቸው፡፡ የፀሐይ መውጣት የመወለድ÷ የፀሐይ መጥለቅ የመሞት÷ ከጠለቀች በኋላም እንደገና መውጣት የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡

         ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙታን እንደሚነሡ በቃልም በተግባርም አስተምሯል፡፡ በቃል ፡- «በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ÷ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ፡፡» ሲል አስተምሯል፡፡ ዮሐ ፭÷፳፱፡፡ በተግባርም የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን አስነሥቷል፡፡ ዮሐ ፲፩÷፵፫፡፡ ቅዱሳን ነቢያት፡- እነ ኢሳይያስ «ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፥ ሬሳዎችም ይነሣሉ፡፡» ብለዋል። ኢሳ ፳፮÷፲፱፡፡ እነ ዳንኤልም፡- «በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች (ሁሉም) ይነቃሉ፤ እኵሌቶችም ወደ ዘላለም ሕይወት÷ እኵሌቶችም ወደ እፍረትና ዘላለም ጉስቊልና፡፡» ብለዋል፡፡ ዳን ፲፪÷፪፡፡ በተለይም ለነቢዩ ለሕዝቅኤል፥ እግዚ አብሔር፦ በአፅም የተሞላ ታላቅ ሸለቆ ካሳየው በኋላ፥ «እነዚህ የደረቁ አጥንቶች ተመልሰው በሕይወት የሚኖሩ ይመስ ልሃልን?» ሲል ጠይቆታል፡፡ ሕዝቅኤልም፡- «እግዚአብሔር ሆይ÷ አንተ ታውቃለህ፤» የሚል መልስ ሰጥቶቷል፡፡ በመጨ ረሻም እነዚህ ሁሉ ሕይወት ዘርተው ሲነሡ አይቷል፡፡ ይኸንንም፡- «እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ÷ ትንፋሽም ገባባቸው፥ ሕያዋንም ሆኑ÷ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ፡፡» በማለት ገልጦታል፡፡ ሕዝ ፴፯፥፩-፲፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሙታን ትንሣኤ በሚገባ ቋንቋ አብራርቶ በምሳሌ ሲያስተምር «ነገር ግን ሰው፥ ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል፡፡» ብሎ ከጠየቀ በኋላ፥ «አንተ ሞኝ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፡፡» ብሏል፡፡ ከዚህም አያይዞ «የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው፡፡ በመበስበስ ይዘራል÷ ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል÷ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል÷ መንፈሳዊ አካል ይነሣል ፤ ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ፡፡ እንዲሁ ደግሞ፡- ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም (ክርስቶስ) ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው። ሁለተኛው ሰው ( ክርስቶስ ) ከሰማይ ነው፡፡ መሬታዊው እንደሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲህ ናቸው÷ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው ፡፡ የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን፡፡» ብሏል። ፩ኛቆሮ ፲፭÷፴፭-፵፱፡፡ በፊልጵስዩስ መልእክቱም፡- «ክቡር ሥጋውን እንደሚስል የተዋረ ደውን ሥጋችንን ይለውጣል፡፡» ብሏል፡፡ ፊል ፫÷፳፩። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም፡- «እርሱን እንድንመስል እናውቃለን፤» ብሏል፡፡ ፩ኛ ዮሐ ፫÷፪።

፩፥፲፪፦ የትንሣኤ ጸጋ፤

         በክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘነው ጸጋ ታላቅ ነው። ከጨለማ ወደ ብርሃን ወጥተናል÷ ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግረናል ። ሙታን የነበርን ሕያዋን÷ ምድራውያን የነበርን ሰማያውያን÷ ሥጋውያን የነበርን መንፈሳውያን ሆነናል፡፡ «ሞት ሆይ÷ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ÷ ድል መንሣትህ የት አለ?» የምንል ሆነናል፡፡ ሆሴ ፲፫÷፲፬ ፣ ፩ኛቆሮ ፲÷፶፭፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ «እኛ አገራችን በሰማይ ነውና÷ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠ ባበቃለን፤ እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋች ንን ይለውጣል፡፡» የምንል ሆነናል፤ ፊል ፫፥ ፳-፳፩፡፡ ናፍቆታችን ሁሉ በትንሣኤ ያገኘነውን ጸጋ እውን ማድረግ ነው፡፡ «ድንኳን የሚሆነው ምድራዊው መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና፡፡ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና÷ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድን ለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም፡፡» ይላል፡፡ ፪ኛቆሮ ፭፥፩-፪፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፡- «ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ÷ እድፈትም ለሌለበት÷ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ይባረክ» ብሏል፡፡ ፩ኛጴጥ ፩÷፫፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም፡- «በሚመጡ ዘመ ናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳ የን ዘንድ ከእርሱ ጋር አስነ ሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊው ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።» ብሏል። ኤፌ፪÷፮-፯። የእግዚአብሔር ቸርነት የድ ንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን ፡

Friday, April 26, 2013

ሆሣዕና


ሆሣዕና እና ምሳሌነቱ
ማቴ 21፡1-10


ሆሣዕና ማለት መድሃኒት ማለት ነው፡፡
ደብረ ዘይት ወይራ የበዛበት ተራራ ነው፡፡
ቤተ ሳጌ የድሆች መንደር ናት፡- ጌታ የድሆች መንደር ወደደ፡፡እኛ ድሆቹን ባለ ፀጋ ሊያደርገን ስለኛ ብሎ ራሱን ድሃ ያደረገ አምላክ ነውና፡፡
ቤተ ሳጌ ለእየሩሳሌም በጣም ቅርብ ናት፡፡እኛም ለቤተ ክርስትያን ቅርብ መሆን አለብን፡፡
እየሩ ሳሌም ቤተ ክርስትያን ናት እንቅረባት 
እየሩ ሳሌም እመቤታችን ናት እንቅረባት
ጌታ ቤተሳጌ በደረሰ ጊዜ የተመሳቀለ መንገድ ቁሞ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱ ላከ
*ሁሩ ሃገረ ቅድመክሙ* ወደ ፊታችሁ ላለው ሃገር ሂዱ ወደ መንደሪቱ ግቡ አላቸው፡፡ 

በተመሳቀለ ቦታ መቆሙ፡- ወደ ፊት በመስቀል ላይ እሰቀላለሁ ሲል ነው፡፡
ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ሲልካቸው በፊታችሁ ላለው ሃገር ሂዱ ያን ጊዜ አህያ ከውርንጭላዋ ጋር ታስራ ታገኛላችሁ ፈታችሁ አምጡልኝ አላቸው፡፡ 

ጌታችን ብዙ ያልታሰሩ አህዮች እያሉ ለምን የታሰሩትን መረጠ?

አህዮቹ የታሰሩት ሌባ ሰርቆ ነው ያሰራቸው፡፡ ወንበዴ ሰርቆ ነው ያሰራቸው 
አህዮቹ ለጌታ ውለታ ሰርተዋል፡፡ ጌታ ሲወለድ አሙቀውታልና፡፡ ለጌታ ውለታ ልንመልስ ያልቻልነው እኛ ሰዎች ብቻ ነን፡፡

የታሰሩት እዲፈቱ የመረጠበት ሚስጥር

እኔ ከሃጥአታችሁ ልፈታችሁ የመጣሁ ነኝ ሲል ነው፡፡
ወንበዴው አህዮቹን ሰርቆ በመንደር እንዳሰራቸው ዲያብሎስም ለሰው ልጅ በሃጥአት ሰንሰለት ከሲኦል መንደር አስራቸው ነበርና፡፡
ሃዋርያቱ ሲልካቸው ምን ታደርጋላችሁ የሚላችሁ ሰው ቢኖር ጌታቸው ይሻቸዋል በልዋቸው አላቸው፡፡ የፈጠራቸው እሱ ነውና፡፡ 

ከአህያዋ ጀርባ ሃዋርያት ልብሳቸው አነጠፉለት ለምን?

ለምንስ ኮርቻ አላደረጉለትም? ለምንስ ልብሳቸው መረጡ? 
ለስላሳ ህግ የሰራህልን አንተ አባት ነህ ሲሉ ነው
ለስላሳ ህግ የተባለው ወንጌል ነው
ወንጌል ፍቅር ናት የሚረግማችሁ መርቁ ትላለችና፡፡
ልብስ የሰውነት ነውር ይሸፍናል፡፡ ነውረ ሃጥአታችን የምትሸፍንልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡ እሱ ልብሳችን ነውና፡፡ ነውራችን የሚሸፍንልን እሱ ነውና፡፡
ችግሩ ግን ነውረ ሃጥአታችን የሚሸፍንልን ልብስ እርሱ መሆኑን አለማወቃችን ነው፡፡
አብሮን እንዳለ አለማስተዋላችን ነው፡፡ 
ስለዚ እደ ሃዋርያት ነውረ ሃጥአታችንን አስቀድመህም የሸፈንክልን ዛሬም የምትሸፍንልን ወደፊትም የምትሸፍንልን አምላክ አንተ ነህ ልንለው ይገባል፡፡

ጌታችን በሁለቱ አህያዎች በጥበብ ተቀመጠ፡- በሰው የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ግን የሚቻል መሆኑ ጥበበኛ አባት ሁሉን የሚችል አባት መሆኑ የሚገልጽ ነው፡፡ አንድም ወንጌልን ኦሪትና ሃዲስን ሁለቱ አስታርቆ አስማምቶ አንዱን አንዱን እየመገበ የሚሄድ መሆኑ የሚያመለክት ነው፡፡

ጌታ ለምን በፈረስ ላይ አልተቀመጠም?

ትንቢትና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡ ት.ዘካ9፡9 ፃዲቅ የባህሪ አምላክ የዋህ ሃዳጊ በቀል ንጉስሽ በአህያ በወርንጭላዋ ተቀምጦ ይመጣል ብላችሁ ለጽዮን ልጅ ንገርዋት ብለዋልና፡፡

ፈረስ
• ተንኮለኛ ናት ለጠላትዋም አውድቃ ረግጣ ትገድላለች
• ረጋ ብላ መሄድ አትችልም ትቸኩላለች
• ልትወጣባት ስትልም ታስቸግራለች አትመችም ተነጣጥረህ ነው የምትወጣባት 
• ጌታ የወደደውና በትንቢቱም እደተገለጸው አህያን መረጠ፡፡

በአህያ መቀመጡ
• ትህትናን ለማስተማር
• የሰላም ዘመን ነው ሲል 
• ለፈለጉኝ ሁሉ የቅርብ አምላክ ነኝ ሲል በንጽህና በየዋህነት ለሚኖሩ መእመናን አድሬባቸው እኖራለሁ ሲል፡፡
• አህያዎች ትሁታን ናቸው ረጋ ብለው ነው የሚሄዱት፤በቀላሉ ትወጣበታለህ፤በቀላሉ ትይዘዋለህ፤እንደፈለክም ታዝዋለህ፤እኛ በትእቢት ተይዘን ነው እንጂ በየዋህነት ብንመላለስ እሱ ያድርብን ነበር፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ማደርያ ነንና፡፡

ትልቅዋ አህያ የኦሪት ምሳሌ ነው
1. ትልቅዋ አህያ ሸክም የለመደች ናት ህገ ኦሪትም የተለመደች ህግ ናትና፡፡
2. የእስራኤል ምሳሌ ነው፡-ትልቅዋ አህያ ሸክም እንደለመደች ሁሉ እስራኤልም ህግ ለመፈጸም በህግ ለመራመድ የለመዱ ናቸው፡፡
3. የአዳም ምሳሌ ነው፡- አዳም ሸክም የበዛበት ነበርና 

ውርጭላዋ
1. በህገ ወንጌል ትመሰላለች፡-ምክንያቱም ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰረታት የሰራት አዲስዋ ህግ ናትና፡፡
2. በአህዛብ ትመሰላለች፡-ትንሽዋ አህያ ሸክም የለመደች አይደለችም እንዲሁም አህዛብም ህግህን የመቀበል የለመደ አይደሉም፡፡ ለህግህ አዲስ ናቸውና፡፡
3. የእመቤታችን ምሳሌ ናት፡- የዓለም ሸክም አቅልላለችና በእመቤታችን ትመሰለላለች፡፡ እመቤታችን ድህነተ ምክንያታችን ጌታን የተሸከመች ንጽህት እንከን የሌላት እናት ናትና፡፡


ህዝቡም ልብሳቸው እያወለቁ በጎዳና አነጡፉለት ለምን?

እንኮን አንተ የተቀመጥክባት አህያም ክብር ይገባታል ብለው ነው፡፡ 
እስራኤላውያን ጌታ የተቀመጠባት አህያ አከበሩ፡፡ ይህ ትውልድ ግን ጌታ የተቀመጠባት እመቤታችን ማክበር ተሳናቸው፡፡
ልብሳቸው ማንጠፋቸው፡- ለክብሩ መግለጫ ነው፡፡

ሌሎችም ቅጠል አነጠፉለት፡ ሶስት አይነት ቅጠል አነጠፉለት
ዝንባባ፤የቴመር ዛፍ፤የወይራ ዛፍ አነጠፉለት፡፡


ዝንባባ
1. ዝንባባ፡- ይስሃቅ በተወለደ ጊዜ ደስ ብሎት አብርሃምን ዝንባባ ይዞ እግዚአብሔር አመስግነዋል፡፡
2. ዝንባባ ደርቆ እንደገና ሂወት ይዘራል፡- የደረቀ ሂወታችን የምታለመልም አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
3. ዝንባባ የሰላም ምልክት ነው፡- የሰላም አምላክ ነህ ሲሉ ነው
4. ዝንባባ የደስታ መግለጫ ነው፡- አንተ ደስ የምታሰኝ ሃዘናችንም የምታርቅልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
5. ዝንባባ እሾሃማ ነው፡- አንተ ህያው አሸናፊ አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
6. ዝንባባ እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል እንጂ፡፡ ጌታም አንተ ባህሪህን የማይመረመር ነው ሲሉ ነው፡፡

የቴምር ዛፍ፡-
1. የቴምር ፍሬ መራራ ጣፋጭም ነው፡- በሃጥአት የመረረውን ሂወታችን የምታጣፍጥልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
2. የቴምር ዛፍ ከፍ ያለ ነው፡-አንተ አምላካችን ልዑለ ባህሪ ነህ፡፡ ከፍ ከፍ ያልክ አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
3. የቴምር ፍሬ በውስጡ ያለውን አንድ ነው፡-አንድ አካል አንድ ባህሪ ነህ ሲሉ ነው፡፡
4. የቴምር ፍሬው በእሾህ የተከበበ ነው፡- ይህም የአንተ ባህሪ የማይመረመር በእሳት የተከበበ ነው ሲሉ ነው፡፡ 


የወይራ ቅርንጫፍ ዛፍ
1. የወይራ ቅጠል ከእንጨት ሁሉ ጽኑ ነው፡፡ አንተም ጽኑ ሃያል አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
2. ወይራ ለመብራት ያገለግላል ዜት ያወጣል፡- ከወይራ የሚገኝ ዘይት ጨለማን አሸንፎ ብርሃን እንደሚሰጥ ሁሉ አንተም ጨለማ ሂወታችን የምታስወግድልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
3. በኦሪት ጊዜ ከወይራ የተገኘ ዘይት ለመስዋእትነት ይቀርብ ነበር፡፡ አንተም እንደ ዘይቱ ለመስዋእት የምትቀርብ አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡ በመስቀል ላይ መስዋእት ሁነዋልና፡፡


ሆሣዕና በእጃችን እደ ቀለበት ማሰራችን የምን ምሳሌ ነው?

1. ጌታ ለአዳም የሰጠው ቃል ኪዳን ለማስታወስ፡-ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድነሃለሁ ያለውን የተስፋ ቃል ለማስታወስ፡፡
2. ጌታ ለእመቤታችን የገባላትን ቃል ኪዳን ተምሳሌት ነው
3. ጌታ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ቃል ኪዳን ተምሳሌት ነው
4. ጌታ ለአዳም ከሰይጣን ግዛት ነጻ እንዳወጣው ሁሉ እኛም ከሰይጣን ግዛት ከመከራ ስጋ ከመከራ ነፍስ ከክፋት ከሃጥአት አውጣን ማረን ለንስሃ ሞት አብቃን ከቤትህ አትለየን እንደ ቸርነትህ ይቅር በላን ስንል ከጌታ ደግመን ላናጠፋ ቃል የምንገባበት ነው፡፡
ስለዚ እንደ ታሰሩ አህዮች መፈታት አለብን፡፡ ሁላችን ታስረናልና ቤተ ክርስትያን በመሄድ እንድንፈታ እናድርግ፡፡ የታሰሩት ሁሉ በካህናት አባቶቻችን አማካኝነት እዲፈቱ ልናድርግ ይገባናል፡፡ ለምን ቢባል አምላካችን ይፈልገናል አባታችን አማላካን ንጉሳችን ይፈልገናል፡፡ ጌታ ጸጋውን አብዝቶ ለዘላለሙ ከቤቱ አይለየን የነጻነት አባት ካለን ሱስና ልማድ ሁሉ ነጻ አድርጎ ለሱ እንድንገዛ እርሱ ይርዳን አሜን መልካም በዓል፡፡

ኒቆዲሞስ



ክርስቲያን ፊደል- ኒቆዲሞ
ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ የምስራቹን ቃል ሲያውጅ እስራኤላውያን የተቀበሉት በተደበላለቀ ስሜት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ሕዝቡ ለብዙ ዘመናት በባርነት ሲገዛ ስለነበር ከሮማውያን ቅኝ ግዛት ነጻ የሚያወጣቸው መሲህ ይፈልጋሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ ለብዙ ዘመናት በባርነት ቀንበር ስለደከመ ተስፋ በመቁረጥ ተዳክሞ ነበር፡፡ መሲህ ቢመጣ እንኳ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት ጦር ይዞ ሰራዊት አስከትሎ ነው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው ክርስቶስን መሲህ ነኝ ብሎ ሲመጣ ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጦር ሳይዝ ሰራዊት ሳያስከትል እንዲሁ ባዶ እጁን አርነት ላወጣችሁ መጥቻለሁ እያለ ደጋግሞ ተናግሯልና ነው፡፡ ምንም እንኳ አብዛኛው እስራኤላዊ የክርስቶስን መሲህነት ቢጠራጠርና ባይቀበለውም፣ በፍጹም እምነት እስከ መጨረሻው የተከተሉትም ነበሩ፡፡ ለዚህም ትልቅ ማሳያ የሚሆነን ከፈሪሳውያን ወገን የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አይሁዳዊ ነው፡፡ቅድስት ቤተክርስቲያንም ይህን ታላቅ ሰው ለማዘከር የዐቢይን ጾም ሰባተኛ እሁድ በእርሱ ስም ሰይማ ታከብረዋለች ፡፡ ተከታዮቿ ምዕመናንም የእርሱን አሰረ ፍኖት እንዲከተሉ ትመክራለች ታስተምራለችም፡፡
ኒቆዲሞስ ማነው?

፩. ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ነው ዮሐ 3-1
የእስራኤላዊያን ለብዙ ዘመን በባርነት መኖር የሕዝቡን የአኗኗር ሁኔታ ቀይሮታል፡፡በግዞት ጊዜ ከአሕዛብ የቀሰሟቸው አጉል ትምህርቶች በእምነትም በአስተሳሰብም እጅግ እንዲለያዩና እንዲራራቁ ምክንያት ሆኗል፡፡ አይሁዳዊ ሳምራዊ፤ ከአይሁድም ሰዱቃዊ ፣ ፈሪሳዊ ፣ ጸሐፍት ፣ ኤሴያዊ ብለው እንዲከፋፈሉ ከዚህም እጅግ ወርደው ገሊላዊ ናዝራዊ እንዲባባሉ ያበቃቸው ከአህዛብ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ፈር ባለማስያዛቸው ነበር፡፡ ፈሪሳዊያን ደግሞ ሕግን በማጥበቅ ሕዝቡን የሚያስመርሩ ቀሚሳቸውን በማስረዘም እነሱ የማይፈጽሙትን ሕግ በሕዝብ ላይ የሚጭኑ ራሳቸውን ከሌሎች በላይ ከፍ ከፍ የሚያደርጉ አባታችን አብርሐም እያሉ የሚመጻደቁ የአባታቸው የአብርሐምን ስራ ግን የማይሰሩ ክፍሎች ናቸው ዮሐ 8-39፡፡ ታዲያ ኒቆዲሞስ ምንም እንኳ ከፈሪሳዊያን ወገን ቢሆንም ራሱን ከዚህ ሕዝብ ለይቶ ክርስቶስን ፍለጋ በፍጹም ልቡ የመጣ ፈሪሳዊ ነው፡፡ ቀድሞ አባታችን አብርሀምን ከቤተሰብህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ ያለው አምላክ ኒቆዲሞስን ከፈሪሳዊያን ለይቶ ጠራው፡፡ ዘፍ 12

፪. ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ ነው ዮሐ 3-1

ሮማውያን ሕዝቡን የሚያሥተዳድሩት ከላይ ያለውን ዋና ሥልጣን ተቆናጠው ታች ያለውን ሕዝብ ደግሞ ባህላቸውን በሚያውቅ ቋንቋቸውን በሚጠነቅቅ አይሁዳዊ ምስለኔ ነው፡፡ አውሮፓውያንም አፍሪካን ለመቀራመት የተጠቀሙበት ስልት ይህን ዓይነት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስም ምንም እንኳ ፈሪሳዊ ቢሆን አለቃ እንዲሆን በሮማውያን የተሾመ ባለሥልጣን ነው፡፡

፫. ኒቆዲሞስ መምህረ እስራኤል ነው ዮሐ 3-10

ጌታ ምስጢረ ጥምቀትን በገለጸለት ጊዜ ሲደናገር አይቶ «አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን? » ብሎታል፡፡ ይህ የሚጠቁመን ኒቆዲሞስ አለቅነትን ከመምህርነት የያዘ በአይሁዳውያን የታፈረና የተከበረ ሰው እንደነበረ ነው፡፡ መምህር ቢሆንም የሚቀረኝ ያላወቅሁት ያልጠነቀቅሁት ብዙ ነገር አለ በማለት የመምህርነቱን ካባ አውልቆ የተማሪነትን ዳባ ለብሶ ከክርስቶስ ሊማር መጣ፡፡

፬. ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት ነው ዮሐ 7-51
አንዳንዴ ሳያውቁ አወቅን ሳይማሩ እናስተምር የሚሉ ደፋር መምህራን አይጠፉም፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ከዚህ በተለየ አለቅነትን ከመምህርነት መምህርነትን ከምሁርነት አስተባብሮ የያዘ ዕውቀትን ከትህትና ምሁርነትን ከደፋርነት አንድ አድርጎ የያዘ ሰው ነበር፡፡ የኦሪት ምሁር መሆኑን የሚጠቁመን ደግሞ ከካህናት አለቆች ጋር ያደረገውን ክርክር ባስታወስን ጊዜ ነው፡፡

ኒቆዲሞስ ምን አደረገ?

ለምስጢረ ጥምቀት መገለጥ ምክንያት ሆነ ዮሐ 3 1-21

የአይሁድ የፋሲካ በዓል እየቀረበ ሲመጣ ክርስቶስ ቀኑ እንደደረሰ ለሐዋርያቱ ተናግሮ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡ እንደ ሰውነቱ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይል ሕዝቡን ቀንና ሌሊት በትምህርትና በተዐምራት ያገለግል ነበር፡፡ በዚህ ሰዐት ነው ኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው፡፡ በፊቱ ቀርቦም «መምህር ሆይ » ብሎ የእርሱን አላዋቂነት የክርስቶስን ማእምረ ኅቡዐትነት (የተሰወረን አዋቂነት) መሰከረ፡፡ ጌታችንም አመጣጡ ከልብ መሆኑን አውቆ ምሥጢረ ጥምቀትን (ዳግም ውልደትን) ገለጸለት፡፡ ምስጢሩ የኦሪት ምሁር ለነበረው ኒቆዲሞስ ለጆሮ የከበደ ለመቀበል የሚቸግር ሆነበት፡፡ የከበደውን የሚያቀል የጠበበውን የሚያሰፋ አምላክ ምሥጢሩ ለኒቆዲሞስ እንደከበደው ስለተረዳ ቀለል አደረገለት፡፡ ዳግም ውልደት ከእናት ማኅፀን ሳይሆን ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ እንደሆነ አብራራለት ፡፡

አዋቂ ነን የሚሉትን አሳፈራቸው ዮሐ 7-51

ወቅቱ የአይሁድ የፋሲካ በዓል የቀረበበት ጻፎችና የካህናት አለቆች ጌታን ለመያዝ፣ እንደሙሴም ህግ ሊያስፈርዱበት የቋመጡበት ጊዜ ነበር፡፡ የሙሴ ፈጣሪ መሆኑን መቸ አወቁና? የካህናት አለቆች ተሰብስበው ክርስቶስን ለመያዝ በሚመካከሩ ጊዜ ከሙሴ መጽሐፍ ሕግ ጠቅሶ ሊቃውንተ ኦሪትን አፍ ያስያዛቸው እሱ ነበር፡፡በዚህም የተነሳ ሳይስማሙ ወደየቤታቸው እንዲበታተኑ ምክንያት የሆነ ታላቅ ሰው ነው፡፡

ጌታን ለመገነዝ በቃ ዮሐ 19-38

ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ ራሱን ለዓለሙ ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ እስከ ሞት ከአንተ አንለይህም ያሉት ደቀ መዛሙርቱ ሲበታተኑ ፣ከዮሐንስ በቀር ፣በዘጠኝ ሰዐት ቀራንዮ የነበረ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ሆኖ የክርስቶስን ስጋ ከአለቆች ለምኖ፣ የገነዘ፣የክርስቶስን ክቡር ሥጋ ከርቤና የእሬት ቅልቅል ያርከፈከፈለት ወደ ሐዲስ መቃብር ያወረደውም ኒቆዲሞስ ነበር፡፡
ከኒቆዲሞስ ምን እንማር?

አትኅቶ ርእስ

በቅዱስ ወንጌል ላይ በተደጋጋሚ የምናገኘው የፈሪሳውያንን ግብዝነትና የጌታችንን ተግሳጽ ነው፡፡ ማቴ 9 10፣ ማቴ 23፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነን የፈሪሳዊውና የቀራጩ ጸሎት ምን ይመስል እንደነበር መመልከት ነው ሉቃ 18 9፡፡ ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ፣ የአይሁድ አለቃ ፣መምህረ እስራኤል ፣ምሁረ ኦሪት ቢሆንም ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታ እግር ስር ቁጭ አለ፡፡ ሕዝብን ከመምራትና ከማስተማር ይልቅ ቁጭ ብሎ መማር ምንኛ መታደል ነው! ጌታስ በትምህርቱ «ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርሷም አይወሰድባትም » ያለ ለዚህ አይደል ሉቃ 10 42፡፡ ብዙዎቻችን ባለን የኑሮ ደረጃ የዕውቀት ደረጃ የስልጣን ደረጃ ራሳችን ሰቅለን የመማር አቅም አጥተናል፡፡ ቁጭ ብሎ መማር ደረጃችንን የማይመጥን የሚመስለንስ ስንቶች እንሆን? አንድ ወቅት አባ መቃርስ ከህጻናት እንቆቅልሽ ለመማር ቁጭ እንዳሉ በእንቆቅልሹም ልባቸው ተነክቶ እያነቡ ወደ በዐታቸው መመለሳቸውን እያወቅን የመማር አቅም ያጣን ስንቶች እንሆን? ማን ያውቃል ከአንድ ሰአት ስብከት ውስጥ እግዚአብሔር ሊያስተመረን የፈለገ አንዲት ዐረፍተ ነገር ቢሆንስ? ትሑት የሚያሰኘው ሳያውቁ አላውቅም ማለት ሳይሆን እያወቁ አላውቅም ማለት ነው፡፡ ሳይማሩ ተምሬያለሁ ማለት ሳይሆን ተምረውም ልክ እንደ ኒቆዲሞስ ለመማር ራስን ዝቅ ማድረግ ነው፡፡

ጎደሎን ማወቅ

መምህርም ምሁርም ሆኖ ቁጭ ብሎ መማር ምን ረብ አለው? ይባል ይሆናል፡፡ ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት እንጅ ምሁረ ሐዲስ አይደለም ኒቆዲሞስ መምህረ እስራኤል ዘስጋ እንጅ መምህረ እስራኤል ዘነፍስ አይደለም፡ ክርስትና አለቃና ባሪያን አንድ እንደምታደርግ አያውቅምና የጎደለውን ፍለጋ መጣ ገላ 3 26፡፡ ያለውን ሳይሆን ያጣውን የሞላለትን ሳይሆን የጎደለውን ፍለጋ መጣ፡፡ዕውቀት ብቻውን ምሉእ አያደርግም፡፡ አለቅነትም ቢሆን ገደብ አለው፡፡የሕይወቱን ክፍተት ሊሞላ የሚችል አንድ ክርስቶስ ብቻ ነውና ጎደሎነቱን አምኖ መጣ፡፡ የሚጎድለኝ ምንድን ነው? ብሎ እንደጠየቀው እንደዚያ ሰው ጎደሎን ማመን ምንኛ ታላቅ ነገር ነው ማቴ 18 21፡፡ በአብዛኞቻችን የሚታየውና ክርስትናችንን አገልግሎታችንን ቤተክርስትያናችንን እየተፈታተነ ያለ ችግር ጎደሎዎቻችንን አለማወቅና ምሉእ ነኝ ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ምንም እንዳልሆኑ አውቆ ራስን ለክርስቶስ፣ ራስን ለመርዐተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አሳልፎ መስጠት ምንኛ መታደል ነው!

አልዕሎ ልቡና (ልቡናንን ከፍ ማድረግ)

ኒቆዲሞስ ይዞ የመጣው ስጋዊ ህዋሳቱን ነበር፡፡ጌታችን ግን አመጣጡ ለመልካም እንደሆነ አውቆ ለስጋዊ ዕውቀት እጅግ የሚከብደውን ምስጢረ ጥምቀትን ገለጸለት፡፡ መጀመሪያ ይህን ምስጢር ለመቀበል አልተቻለውም ነበር፡፡ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ምስጢሩን ፍንትው አድርጎ ሲያብራራለት ግን ልቡናው ይህን ምስጢር ለመቀበል ከፍ ከፍ አለ፡፡ ምስጢራትን ለመቀበል ልቦናን ከፍ ከፍ ማድረግ ይገባል፡፡የእምነታች መሰረት በስጋ ዓይን ማየት በስጋ ጆሮ መስማት በስጋ እጅ መዳሰስ ብቻ ከሆነ ልክ እንደ እንቦይ ካብ ሆነ ማለት ነው፡፡ ትንሽ ነፋስ ትንሽ ተፅዕኖ ሲያርፍበት መፈራረስ መናድ ይጀምራል፡፡ ኒቆዲሞስም ምስጢሩ መጀመሪያ ቢከብደውም ቅሉ በኋላ ላይ ልቦናውን ወደ ሰማያዊው ምስጢር ከፍ ስላደረገ ምስጢሩ ተገለጸለት፡፡ ቤተክርስቲያንን ሲፈታተኗትና እየተፈታተኗት ያሉ አካላት በሙሉ የስህተታቸው ምንጭ እንደ ግያዝ ከአካባቢያቸውና ከምናየው አካል (ቁሳዊ ዓለም) ውጭ መመልከት አለመቻል ነው 2ነገ 6- 17፡፡ ለዚህም ነው ካህኑ በስርዓተ ቅዳሴ ጊዜ የቁርባኑ ምስጢር እንዲገለጽልን «አልዕሉ አልባቢክሙ (ልቦናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ)» የሚሉን፡፡

የእውነት ምስክር (ስምዐ ጽድቅ) መሆን

ኒቆዲሞስ ያለፍርሐትና ያለ ሃፍረት በካህናቱ ፊት እውነትን መስክሯል፡፡እውነትንና ፀሐይን ፈርቶ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ካህናቱን መጽሐፍ ጠቅሶ እውነትን ተናግሮ አሳፍሯቸዋል፡፡ በመሪዎች ፊት በታላላቅ ሰዎች ፊት እውነትን መመስከር ክርስትናችን የሚያስገድደን ቁም ነገር ነው ሉቃ 12 8፡፡ ቤተክርስቲያን ሰማዕታት እያለች የምትዘክራቸው በሙሉ ለእውነት ብለው ራሳቸውን ለክርስቶስ አሳልፈው የሰጡ ቅዱሳንን ነው፡፡በፍርሐትና በሀፍረት በይሉኝታና በሀዘኔታ እውነትን አለመመስከር በክርስቶስ ፊት ያስጠይቃል እንጅ አያስመሰግንም ማቴ 10 32፡፡ «ለእውነት እንጅ በእውነት ላይ ምንም ማድረግ አንችልም» እንዳለ 2ቆር 13 8፡፡

ትግሃ ሌሊት

እንደ ሌሊት ለመንፈሳዊ ህሊና ለተመስጦ የሚመች ጊዜ የለም ፡፡ ቀን ለስጋ ሲራወጥ የነበረ አካልና መንፈስ ሌሊቱን ለነፍስ በምገዛት ስጋውን መጎሰም አለበት፡፡ ለዚህም ነው ቅድስት ቤተክርስቲያን ቀኑን በቅዳሴ ሌሊቱን ደግሞ በማኅሌት በሰዓታት በኪዳን እግዚአብሔርን ስታምሰግን የምታድረው፡፡ ቅዱስ ማር ይስሐቅ ሌሊትስ ጌታን ለማመስገን የተፈጠረ ድንቅ ጊዜ ነው ያለው፡፡ ጌታችንም ሐዋርያቱን ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ ብሏቸዋል ማቴ 26፡፡ አሁንም ቤተክርስቲያን እንደ ኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ ለኪዳን ለማኅሌት ለጸሎት የሚመጣን ምዕመን ትፈልጋለች፡፡

እስከ መጨረሻ መጽናት

ጌታችንን በመዋዕለ ስብከቱ ብዙ ሺህ ሕዝብ ቢከተለውም እስከመስቀሉ አብረውት የነበሩ ጥቂቶች ናቸው፡፡ የተወሰነው ሕዝብ ቀድሞም የተከተለው ለምግበ ስጋ ነበርና ቀራንዮ ላይ አልተገኘም፡፡ ቀራንዮ ላይ ምግበ ነፍስ እንጅ ምግበ ስጋ የለም፡፡ ሌሎችም በቤተሰብ በሀብት በፍርሀት ምክንያትነት መስቀሉ ስር አልተገኙም፡፡ ምንም እንኳ ኒቆዲሞስ በስድስት ሰዐት ባይገኝም የክርስቶስ ስጋ ከነፍሱ በምትለይበት ሰዐት ክርስቶስን ከመስቀል አውርዶ ለሐዲስ መቃብር ያበቃው እሱ ነበር፡፡ በዚህ የመከራ ሰዐት ከዮሐንስና ከእናቱ ከድንግል ማርያም ውጭ ማንም እንዳልነበረ መጻሕፍት ከገለጹልን በኋላ የምናገኛቸው የቁርጥ ቀን ልጆች ዮሴፍንና ኒቆዲሞስን ነው፡፡ ይህም ፈተናውን ሁሉ ተቋቁሞ እስከ መጨረሻው ለመጽናቱ ምስክር ነው፡፡ በክርስትና ሕይወታችንም የምናያቸው ነገሮች ከዚህ የተለዩ አይደሉም፡፡በምቹ ጊዜ የምናገለግል ፈተና ሲመጣ ጨርቃችን(አገልግሎታችንን) ጥለን የምንሮጥ ማር 14-51 ሰበብ አስባብ ፈልገን የምናፈገፍግ ብዙዎች ነን፡፡ ዕውቀት ጣዖት ሆኖበት መሀል መንገድ የቀረው ሀብት ጣዖት ሆኖበት ሩጫ ያቋረጠውን ጊዜ ጣዖት ሆኖበት ቅዳሴ የሚቀረውን ቆጥረን እንጨርሰው ይሆን? ጌታ በትምህርቱ «ለዘአዝለፈ ትዕግስቶ ውእቱ ይድኅን -እስከ መጨረሻው የሚፀና እርሱ ይድናል » እንዳለ ማቴ 2413፡፡ ክርስትና ለጀመሩት ሳይሆን ለጨረሱት ለወጠኑት ሳይሆን ለፈጸሙት የድል አክሊል የምትሰጥ መንገድ እንጅ የመሮጫ መሙን ጠበበን ሩጫው ረዘመብን ለሚሉ ዴማሶች ቦታ የላትም፡፡2ጢሞ 4-9

በአጠቃላይ ከኒቆዲሞስ ህይወት ብዙ ቁምነገሮችን እንማራለን፡፡ የኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ መምጣት ለምስጢረ ጥምቀት ትምህርት መገለጥ ምክንያት እንደሆነ ሁሉ በቅዳሴው በኪዳኑ በሰዓታቱ በማኅሌቱ መገኘትና መሳተፍ ረቂቅ የሆነው ሰማያዊ ምሥጢር ፍንትው ብሎ አንዲገለጥልን ምክንያት ነውና በምሥጢራት በመሳተፍ ራስን ዝቅ በማድረግ ለታላቅ ክብር እንድንበቃ የእርሱ መልካም ፈቃድ ይሁንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ገብርሔር


ዛሬ ታላቁን የጌታችንን ጾም ከጀመርን ስድስተኛ ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህን ሳምንት ቅድስት ቤተክርስቲያን «ገብርሔር» የሚል ስያሜ ሰጥታዋለች፡፡ ገብርሔር በጎ አገልጋይ ማለት ሲሆን የስያሜውን መነሻ የምናገኘው በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው የወንጌል ክፍል ማቴ.25-14-30 ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ መስሎ ካስተማራቸው ትምህርቶች መሀከል አንዱ የሆነው ይህ የዛሬው ወንጌል አስተማሪ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን በውስጡ ይዟል፡፡ በተለይ ምንም እንኳን የቤተክርስቲያን ሓላፊነት የእገሌና የእገሊት ተበሎ ባይወሰንም ቅሉ ቤተክርስቲያን ባላት የአገልግሎት መዋቅር መሠረት የሓላፊነትን ቦታ ይዘው ለሚያገለግሉ ሰዎች አትኩሮት ሊሰጡባቸው የሚገባቸውን ነጥቦች ይጠቁማል፡፡ ይህን ለማየት ያመቸን ዘንድ ከታሪኩ የመጀመያ ክፍል በመነሣት ዋና ዋና የሆኑ አሳቦችን በአትኩሮት መመርመር ጠቃሚ ነው፡፡

በምሳሌያዊው ታሪክ መጀመሪያ ላይ የምናገኘው አንድ መንገድ ሊጀምር ያሰበ ሰው ከመሔዱ በፊት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን ለአንዱ አምስት ለአንዱ ሁለት እንዲሁም ለሌላኛው አንድ መክሊት ነግደው ያተርፉበት ዘንድ እንደሰጣቸው ነው፡፡

ገና ከታሪኩ መጀመሪያ እንደምንረዳው የአገልጋዮቹ ጌታ ምንም እንኳን እርሱ ለመንገድ ቢዘጋጅም ሀብቱ ግን በተዘጋ ቤት ውስጥ ተቆልፎበት እንዲቀመጥ አልፈለገም፡፡ በዚህም አገልጋዮቹን ጠርቶ ገንዘቡን በአደራ ተቀብለው «እንዲያተርፉበት» ማዘዙን እንደማስረጃ ልናቀርብ እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን ማትረፍ በመፈለጉ ብቻ ገንዘቡን ያለአግባብ አልበተነም፡፡ ነገር ግን ለእርሱ ቀረቤታ የነበራቸውን አገልጋዮቹን ጠርቶ ያውም እንደየችሎታቸው መጠን ሓላፊነቱ ሳይከብዳቸው እንዲሠሩበት ገንዘቡን አከፋፈላቸው፡፡

ይህ ጌታ ቅንነትና ርኅራኄ የበዛለት እንደሆነ የሚያመላክተን ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለአገልጋዮቹ ሓላፊነትን ቢሰጥም እንኳን ከእነርሱ ጋር በነበረው ቀረቤታ ማን ምን መሥራት ይችላል የሚለውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዳቸው እንደ ሓላፊነት የመሸከም አቅማቸው አምስት ሁለት አንድ እያደረገ መስጠቱ ነው፡፡

ምናልባት ስስት ባልተላቀቀው ስሜት ለሚያስብ ሰው የዚህ ጌታ መክሊት አሰጣጥ አድልዎ ያለበት ሊመስለው ይችላል፡፡ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ብንከታተለው ግን የሚያሳየን የባለ መክሊቱን ባለቤት ቅንነት ነው፡፡ ቀጥለን እንደምናነበው ይህ ጌታ ለአገልጋዮቹ አትርፉበት ብሎ መክሊቱን ሰጥቷቸው በሔደበት ሀገር አልቀረም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ በተሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው እንደመጣ እናነባለን፡፡ ስለዚህ አገልጋዮቹ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩ እንደሚጠይቃቸው እያወቀ ከአቅማቸው በላይ የሆነ መክሊትን በመስጠት ምን ሠርተው የተሰጣቸውን መክሊት ያህል ማትረፍ እንደሚችሉ በማሰብ እንዲጨነቁ አልፈለገም፡፡ በተቃራኒው የምናየው ያለምንም ጭንቀት ከአእምሯቸው በላይ ሳይሆን ባላቸው ኃይል ተጠቅመው መሥራትና ማትረፍ የሚችሉትን ያህል መክሊት እንደሰጣቸው ነው፡፡

ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው ሲመጣ አምስት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ አምስት እንዲሁም ሁለት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ ሁለት መክሊት አትርፎ ጌታቸው ፊት እንደቆሙ ያ ጌታም በእነዚህ አገልጋዮቹ ታማኝነት ተደስቶ ወደ ደስታው እንዳስገባቸው እናያለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ያ አንድ መክሊት ተቀብሎ የነበረው ምድርን ቆፍሮ ያተርፍባት ዘንድ የተሰጠችውን መክሊት እንደቀበረ ከዚህም አልፎ ምን አደረክባት ተብሎ ሲጠየቅ የአመጽ ንግግር እንደተናገረ በዚህ ከፊቱ ያዘነው ጌታውም ያን ክፉ አገልጋይ እንዲቀጣ እንዳደረገው አናነባለን፡፡

በዚህኛው ክፍል ከተጠቀሰው ታሪክ ሦስቱን አካላት ማለት የመክሊቱን ሰጪ ጌታ፣ በጎ የተባሉ አገልጋዮችና ክፉ እና ሰነፍ የተባለውን አገልጋይ በተናጥል እንመልከታቸው፡፡

1. የአገልጋዮቹ ጌታ፡-

ይህ ሰው ለገንዘቡ ጠንቃቃ ከመሆኑ ባሻገር በአገልጋዮቹ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው እናያለን፡፡ በክፉው አገልጋይ ላይ ባለመታዘዙ ምክንያት የፈረደበትን ፍርድ /ልቅሶና ጥርስ ማፏጨት ወዳለበት በውጪ ወዳለ ጨለማ አውጡት/ ስንመለከት የሚያሳየን የአገልጋዮቹን ጌታ ታላቅ ሥልጣን ነው፡፡ ምንም እንኳን ሥልጣኑ ጽኑ ቢሆንም ይህ ጌታ ፍርዱ ግን በእውነት ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ደግሞ በድካማቸው ታግዘው በተሰጣቸው መክሊት ላተረፉት በጎ አገልጋዮች የሰጣቸውን ፍጹም ደስታ መጥቀስ ይቻላል፡፡

2. በጎ አገልጋዮች:-

በአገልጋዮቹ ጌታ በጎ አገልጋዮች የተባሉት አምስት መክሊት የተቀበለውና ሁለት መክሊት የተቀበለው ናቸው፡፡ እዚህ ጋር ማስተዋል የሚገባው እነዚህ ሁለቱ አገልጋዮች በጎ አገልጋዮች ለመባል ያበቃቸው አስቀድመው ብዙ ወይንም የተሻለ ቁጥር ያለው መክሊት ለመቀበል መብቃታቸው አይደለም፡፡ ጉዳዩ የመክሊቱ ቁጥር ሳይሆን በተሰጣቸው መክሊት መጠን የሚገባቸውን ያህል ደክመው ማትረፍ መቻላቸው ነው፡፡ ወይንም ያ ባለ አንድ መክሊት አገልጋይ ከሁለቱ ያሳነሰው ከአንድ በላይ መክሊት መቀበል የማይችል መሆኑ ሳይሆን በዚያችው በአንዷ መክሊት እንኳን መሥራት አለመቻሉ ነው፡፡

3. ክፉና ሰነፍ አገልጋይ:-

ይህ ሰው የተጠቀሱ ሦስት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡
ሀ. የአገልጋዮቹ ጌታ ወደ መንገድ ሊሔድ በተዘጋጀበት ወቅት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደችሎታቸው ገንዘቡን ሲሰጣቸው አትርፈው እንዲቆዩት ነው፡፡ ከላይ እንደተነገጋገርነው እንደ አቅማቸው መስጠቱም አቅማቸው በሚፈቅደው የሥራ ደረጃ እንዲሰማሩ በማሰብ ነበር፡፡ ይህ ሰነፍ አገልጋይ ግን ያደረገው ከታዘዘበት ዓላማ በተቃራኒው መልኩ ነው፡፡ ሊሠራበት የሚገባውን መክሊት ቀበረው፡፡ ይህም ለጌታው ትዕዛዝ ያለውን ቸልተኝነት ያሳያል፡፡

ለ. ጌታው በመጣ ጊዜ አመጽ የተመላበት የሐሰት ንግግር ተናግሯል፡- ከሔደበት ቦታ ተመልሶ ጌታው በተሰጠው መክሊት ምን እንዳደረገ ሲጠይቀው «አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበሰብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ ስለፈራሁም ሔድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፡፡» ሲል መለሰለት፡፡ ይህ ንግግር ከአመጽ ንግግርነቱ በተጨማሪ ውሸት አለበት፡፡ ምክንያቱም እርሱ እንዳለው ጌታው ካልዘራበት የሚያጭድ ካልበተነበት የሚሰበሰብ ጨካኝ ሰው ቢሆን ኖሮ ያደርግ የነበረው ምንም መክሊት ሳይሰጠው ከነትርፉ ሁለት መክሊቶችን ይጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ተጽፎ የምናነበው ትርፉን ከመጠየቅ በፊት አንድ መክሊት ሰጥቶት እንደበረ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አስቀድሞ ገንዘቡን ዘርቶ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጌታ ዘርቷልና ማጨድ ይገባዋል፤ በትኗልና መሰብሰብም መብቱ ነው፡፡

ሐ. እርሱ መሥራት ሲሳነው እንኳን ዕድሉን ለሌሎች አልሰጠም፡- ይህ ሰው የተሰጠው መክሊት በትርፍ ሊመለስ እንደሚገባው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ምክንያቱም ገና ሲቀበል ከጌታው የተቀበለው ትዕዛዝ ነውና፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን መውጣት መውረዱ ቢከብደውም ወጥተው ወርደው ማትረፍ ለሚችሉ ሰዎች አለመስጠቱ ተጨማሪ ጥፋቱ ነው፡፡ ይህን እንዳያደርግ ያሰረው ደግሞ ውስጡ የተቀረጸው የአመጽ መንፈስ ነው፡፡ ጌታው መጥቶ ስለ ትርፉ ሲጠይቀው የሚመልስለትን ረብ የለሽ ምክንያት እንደ መከላከያ አድርጎ ማሰቡ አእምሮው ሌላ አማራጭ እንዳያስብ የዘጋበት ይመስላል፡፡

የመጽሐፈ ቅዱስ መተርጉማን አባቶች የዚህን ምሳሌያዊ ታሪክ ምስጢር ሲያስተምሩ የአገልጋዮቹ ጌታ የፍጡራን ጌታ የሆነ የእግዚአብሔር ምሳሌ እንደሆነ እንዲሁም ሦስቱ አገልጋዮች በተለያየ ደረጃ ያሉ ምዕመናንን እንደሚወክሉ ያስተምራሉ፡፡

ከዚህ የወንጌል ክፍል ምን እንማራለን?

ከተጠቀሰው ታሪክ የምንማራቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም አበይት የሆኑትን ሁለቱን እንመልከታቸው፡፡

1. ለእያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ እንዳለ እንረዳበታለን

እግዚአብሔር እያንዳንዳችን በሃይማኖት ሆነን የምናፈራውን ፍሬ ይፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን ከእኛ ፍሬን ቢፈልግም ያን ፍሬ ማፍራት የምንችልበትን ኃይል ግን የእግዚአብሔርን ልጅነት ካገኘንበት ከዕለተ ጥምቀት ጀምሮ እንደሚያስፈልገን መጠን እየሰጠን ነው፡፡

ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበልናቸው ስጦታዎች በቁጥር እጅግ ብዙ ቢሆኑም በአይነታቸው ግን ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው እያንዳንዱ ክርስቲያን ዳግመኛ በመወለድ ምስጢር ያገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት ጸጋና ከልጅነት ጋር በተያያዘ የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው ፡፡ዮሐ.3-3 ሁለተኛው አይነት ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና እንደ ሰውየው አቅም ለተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ማስፈፀሚያ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔር የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ትንቢት መናገር ፣ በተለያዩ ልሳናት መናገር ፣ አጋንንትን ማስወጣት ... የመሳሰሉት ከዚህኛው አይነት ስጦታ የሚመደቡ ናቸው፡፡ 1ኛ ቆሮ.12-4፡፡

በመጀመሪያውም ይሁን በሁለተኛው አይነት ስጦታ ተቀባዮች ዘንድ ግን ብዙ የሚያሳዝኑ ችግሮች አሉ፡፡ በዳግመኛ መወለድ ምሥጢር (በ40 ና 80 ቀን ጥምቀት) ስላገኘነው የልጅነት ጸጋ ጊዜ ሰጥቶ የሚያስብ ክርስቲያን ማግኘት በዚህ ዘመን በጣም አዳጋች ነው፡፡ በዓመት ውስጥ ክርስቲያንነቱ ለጥምቀት በዓልና ለመስቀል ደመራ ካልሆነ ትዝ የማይለው ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ከቤተ ዘመድ አንድ ሰው ምናልባትም ራሱም ሊሆን ይችላል ነፍሱ ከሥጋው ካልተለየች ወደ ቤተ ክርስቲያን ደጅ ብቅ አይልም፡፡

እግዚአብሔር ለእኛ የልጅነትን ጸጋ በመስጠቱ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅሩን አሳይቶናል፡፡ ምክንያቱም ልጅነታችን ዋጋ ተከፍሎበታልና፡፡ እንዲሁ በቀላሉ አይደለም ልጆች የተባልነው፡፡ እኛ ልጅነትን እንድንቀበል አምላክ መከራን ተቀብሏል፡፡ የጥምቀታችን ውሃ የፈሰሰው በጦር ከተወጋው ከጌታ ጎን ነው ፡፡ ዮሐ.19-24፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይሄንን ሁሉ ሲያመለክት ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ፡፡›› 1ኛ ዮሐ.3-1 ያለው፡፡

እኛ ልጆቹ እንሆን ዘንድ እግዚአብሔር ካሳየን የአባትነት ፍቅር በተጨማሪ ልጆቹ ስለመሆናችን የገባልንም ተስፋ ከአዕምሮ በላይ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምዕመናን በላከው መልእክቱ ‹‹እንኪያስ እናንተ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፡፡ ልጆች ከሆናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ፡፡›› ገላ.4-7 ስለሚጠብቀን ተስፋ ነግሮናል፡፡

ትልቁ ችግር ግን ተጠማቂው ሰው ይህን የልጅነት ክብር አለመረዳቱ ነው፡፡ የልጅነቴን ክብር ተረድቻለሁ እያለ የሚያወራውም ቢሆን የልጅነቱን መክሊት በልቡናው ውስጥ ቀብሮ አንድም ፍሬ ሳያፈራ ስለማንነቱ ለማውራት ቃላት ሲመርጥ ጊዜውን ያባክናል፡፡ አብዛኛው ግን የክርስትና እምነት ደጋፊ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅነት ሊገለጥ የሚገባው እንደ ሀገር ልጅነታችን በምናሳየው የደጋፊነት /የቲፎዞነት/ ስሜት አይደለም፡፡ ደጋፊነት በጊዜ ና በቦታ ለተወሰነ ያውም ኃላፊ ለሆነ ድርጊት ነው፡፡ ክርስትና ግን በማንኛውም ቦታ፣ ጊዜ የሚኖርበት የህይወት መስመር እንጂ የሚደገፍ ጊዜያዊ ድርጊት አይደለም፡፡

ስለዚህ በጣም ልንጠነቀቅበት የሚገባን የመጀመሪያው መክሊታችን ልጅነታችን መሆኑን መረዳት ያስፈልገናል፡፡በዚህም መክሊት እንድንሰራ የታዘዝናቸውን ምግባራት እንድናፈራ የሚጠበቅብንን ፍሬዎች ማፍራት አለብን፡፡ ያለበለዚያ መክሊቱን እንደቀበረው ሰው መሆናችን ነው፡፡

2. እያንዳንዱ ስጦታ እንደሚያስጠይቅ እንረዳለን

እግዚአብሔር ያለ አንድ አላማ ለሰዎች ኃላፊነትን የሚያሰከትል ስጦታ አልሰጠም አይሰጥምም፡፡ ማንም ከእግዚአብሔር የተቀበለ ሰው የተሰጠው ስጦታ ለሆነ አላማ ነውና ጥያቄ አለበት፡፡ ጠያቂው ደግሞ የስጦታው ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

መንጋውን እንዲጠብቁለት ሥልጣንና የተለያዩ የአገልግሎት ሰጦታዎችን እግዚአብሔር የሰጣቸው አሉ፡፡ዮሐ. 21-15 ፤ ገላ.1-15-16፡፡ ሆኖም ግን የተሰጣቸው ኃላፊነት የሚያስጨንቃቸው፣ ከልባቸው በእውነተኛ ትህትና የሚተጉ ያሉትን ያህል የሚያገለግሉበትን ስጦታ ከእግዚአብሔር መቀበላቸውን እንዲሁም የሚያስጠይቃቸው መሆኑን እስኪዘነጉ ድረስ መንገዳቸውን የሳቱ አሉ፡፡ በእግዚአብሔርና በሰዎች መሀከል እንደ ድልድይ ሆነው ያገለግሉበት ዘንድ በተሰጣቸው ሥልጣን እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ተግባር የሚፈፅሙ ሰዎች ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

እንዲሁም ደግሞ ተሰባኪውን ወደ እግዚአብሔር ከመምራት ይልቅ የነሱ ደጋፊ፣ ስለክብራቸው ተሟጋች እንዲሆን በህዝቡ መሀከል ጎራ እንዲፈጥርና የጳውሎስ ነኝ የአጵሎስ ነኝ እንዲል የሚያደርጉት ሰባኪዎችም ሌሎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ማንም ይሁን ማን ግን ስለተሰጠው መክሊት ባለቤቱ ከፊቱ አቁሞ እንደሚጠይቀው መዘንጋት የለበትም፡፡


በዲ/ን አባተ አስፋ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ደብረ ዘይት

እንኳን ለጾመ እኩሌታው /ለደብረ ዘይት/ በሰላም አደረሳችሁ፡፡
ደብረ ዘይት

ብዙዎች በስሜ ይመጣሉ /ማቴ.24.1-36/


የዐቢይ ጾም አምስተኛው ሳምንት ደብረ ዘይት ይባላል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በደብረዘይት ነገረ ምጽአቱን እንዳስተማረ የሚነገርበት ሳምንት ነው፡፡ «ወእንዘ ይነብር እግዚእነ ውሰተ ደብረዘይት ቀርቡ ኀቤሁ አርዳኢሁ እንተበህቲቶም» ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ስምዖን፣ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ እንድርያስን ጨምሮ ቀርበው «ንገረን ይሄ መቼ ይሆናል?» በማለት ጥያቄ ጠየቁት፡፡ ጥያቄውም የዓለም መጨረሻውና የመምጫህ ምልክቱ ምንድን ነው? የሚል ነበር፡፡
ጌታችንም የዓለም መጨረሻውና ምልክቱን በዝርዝር አስረድቷቸዋል፡፡ እኛም ጊዜው ግድ ከሚለን አንፃር አጠር አድርገን ዋና ዋናዎችን እንመለከታን፡፡

- «ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ እኔ ክርሰቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎች ይስታሉ» የሚለው ኃይለ ቃለ የዓለምን መጨረሻ ከሚጠቁሙን ዋና ምልክቶች መካከል አንዱ የብዙዎች በስሙ መመጣት ነው፡፡ ይህም ከዚህ በፊት በዓለም ላይ ብዘዎች «እኔ ክርስቶስ ነኝ» ብለው የመጡ አሉ፡፡ ከዚህ በከፋ መልኩ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንኳ በየመንደሩ በክርስቶስ ስም የሚፈለፈሉ የእምነት መሳይ ድርጅቶች ዛሬ በሺዎች የሚቆጠሩ ሆነዋል፡፡ ስለዚህ ጌታችን በስሜ ይመጣሉ ማለቱ ለማስጠንቀቂያ በመሆኑ ሰዎች ተሰነካክለው እንዳይወድቁ ለማሳሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ስለ ሃይማኖት እውቀቱም ብቃቱም ሳይኖራቸው ክርሰቶስ በሕልም በራዕይ ተገለጠልኝ በማለት ሰይጣን የሚጫወትባቸው ብዘዎች ስለሆኑ ሌላው ማስተዋል አጥቶ እየተከተላቸው እንዳይስት ነው፡፡ ዛሬ ሰይጣናዊነት /Devilism/ እንኳ ክርስቶስን እንደመከተል የተቆጠረበት ጊዜ ነው፡፡

- «ጦርነም የጦርንም ወሬ ትሰማላችሁ» የኸም የአንድ ሀገር ሕዝብ ከሌላ የሀገር ሕዝብ፤ በአንድ ሀገር ውስጥ እርስ በርሱ በአንድ ቤተሰብ እንዲሁ መለያየትና መዋጋት በዓለም ይሰፍናል፡፡ የአንደኛውና የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ከዚያም በኃላ ያለው እልቂት የምጽአቱን ምልክት ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም የባሰ የእልቂት አይከሰትም ለማለት ምንም ማረጋገጫ የለንም ትንቢቱም የሚለው ይህ ጥቂት መሆኑንና ከዚህም የባሰ የትንቢት ማረጋገጫ መኖሩን ነው፡፡

- ወይም ራሀብ ቸነፍር የምድር መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፡፡ ይህም የሚያሳየው ከሀገራችን ጀምሮ ድሆች ሀገራትን ስንመለከት ረሀብ ይወራባቸዋል፡፡ የምድር መናወጥን ስናይ ለሁሉም ዓለም መኖሩን በየጊዜው የቴሌቨዥን መስኮቶች እያስረዱ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ ሌሎች የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ እልቂቶች በዓለማችን ላይ ሰፍነው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በአደጉ ሀገሮች ላይ የሚታየው የኑሮ ቀውስ ሁሉ የምጽአቱ መቃርብ ምልክት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን ይህ ገና የመጀመሪያው መከራ እንጂ ቀጣዩ ከዚህ የሚበልጥ መሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ ዋነኛው ደግሞ ሰዎች በረሀብ ነፍስ መምታታቸው ነው፡፡ ይህም ዓለም ዛሬ በሚዲያዎቹና በተለያየ መገናኛዎቹ እያደነቀ ያለው ዓለማዊነት በመሆኑ ዓለምን ወደ አንድ ባህል ለማሸጋገር /ግሎባለይዜሽን/ በሚል አሰተሳሰብ እግዚአብሔርን ማመን ትኩረት የማይሰጠው በመሆኑ አሁን ደግሞ መላው ዓለም እግዚአብሔርን እንዲዘነጋ እየተሠራ ነው፡፡ ዓለም ትኩረት የሚሰጠውና የሚያደንቀው ኳስ ተጫዎችን ፊልም ተዋናይን፣ ዘፋኝነትን ወዘተ መሆኑ ጊዜው መቅረቡን ያስረዳል፡፡

በመሆኑም ሰው ከቃለ እግዚአብሔር እጦት የተነሳ በረሀብ ነፍስ እየተጐዳ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህም በመጨረሻ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንድናጣና ገሀነመ እሳት እንድንወድቅ የሚያደርግ ነው፡፡

በተጨማሪም ስለኔ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፣ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኃል ፍቅር ትቀዘቅዛለች፣ ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው ወዘተ.. የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች ያዛሉ መልእክቶች አምላካችን አስተላልፉልናል ይህንንም በዝርዝር ብናይ በውስጣቸው ብዙ መልክቶች እናገኛለን፡፡ ዋናው ቁም ነገሩ ለምልክትነት የሚገለጸውን መከራና የክህደት ዜና ታግሶ በሃይማኖት መጽናት እጀግ ጠቃሚና ለመንግሥት ሰማያት የሚያበቃ ነው፡፡ የእግአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን፡፡ 

በአባ ዘሚካኤል

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Friday, April 19, 2013

ኑ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንስራ መ.ነህ 2:20

ሰላም እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን የተወደዳችው የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ያደራ ልጆች እንደምን ውላችዋል እንደምን አድራችዋል የቅዱስ እግዚአብሔር ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን
ይችን በጅማሬ ያለች ቤተ ክርስቲያንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የእናንተን እርዳታ እሻለን የአቅማችሁን በመርዳት የበረከቱ ተካፋይ እንድትሆኑ በማለት በቅድስት ድንግል ማርያም ስም እ
ማፅናለ ክብር ምስጋና ለመድሓኔአለም ይሁን የእናታችን የቅድስት ቅዱሳን የድንግል ማርያም በረከት ረዴት ከሁላችን ጋር ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን
የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል እኛም ባሪያዎቹ ተነስተን እንሰራለን.መጽ ነህምያ 2:20 —

ይህን ሚስኪን ምንም የሌለው ከ ሰባ የማይበልጡ ክርስትያን ያለዋት ቤተ ክርስትያን የሚሰራላቸው አጥተው በዋርካ ስር ምስለ ፍቅሩ ወልዳ አስቀምጠው ለ32 ዓመታት የኖሩ ወገኖቻችን እንመልከታቸው እንያቸው ከጎናችሁ አለን እንበላቸው፡፡ ህንፃ ቤተክርስቲያኑ እየተሰራ ሲሆን የቤተ ክርስቲያኑን ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በተቸላችሁ መርዳት ይቻላል..

ኑ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንስራ መ.ነህ 2:20… 

ቅዱስ እንጦንስ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር
 Commercial Bank of Ethiopia, Bomb Tera Branch. Account no. 1000017080249
 mobile +251911143653, +251911780816, +251910016008 
ክብር ምስጋና ለመድሓኔአለም ይሁን፡፡ለፍፃሜው አድርሶ የበረከቱ ተካፋይ ለመሆን ያብቃን፡፡በርቱ እመቤቴ ከነልጅዋ ትርዳችሁ ትርዳን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!


 

Tuesday, April 2, 2013

ጉዞ ወደ ላፍቶ ሌንቃ መድሐኔዓለም መጋቢት 22 ቀን በተሳካ ሆኔታ አደረገ፡፡

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! 
የተሳካ መንፈሳዊ ጉዞ 
“የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን” ነህ.2፡20
 በመጀመርያ ይህን ሁሉ ላደረገ ልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው እንላለን!! የቅዱስ እንጦንስ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማህበር ጉዞ ወደ ላፍቶ ሌንቃ መድሐኔዓለም መጋቢት 22 ቀን በተሳካ ሆኔታ አደረገ፡፡ በጉዞው ለተሳተፉ መንፈሳዊ ወንድሞች ፤ እህቶች ፤ እናቶች ፤ አባቶች ፤ህፃናት በጠቅላላ በማህበራችን ስም ምስጋናችንን እያቀረብን በጉዞው ላይ ከተነሱ ፎቶግራፎች ውስጥ የተወሰነውን አፕሎድ አድርገናል ይመልከቱአቸው ፡፡ የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን እዚህ ደርሷል የቀረው የፊኒሺንግ ሥራ ነው፡፡ የመድኃኔዓለምን ቤተ ክርስቲያን በእቃዎችም ሆነ በገንዘብ እንዲሁም በቦታው በመሄድ አገልግሎት በመስጠት ከበረከቱ ተሳታፊ መሆን የምትፈልጉ: የባንክ አካውንት ቁጥር 1000017080249 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መርካቶ፤ ቦንብ ተራ ቅርንጫፍ ቤተክርስቲያኗን በመርዳት በተጨማሪም በየትኛውም ቦታ ያለን ምዕመናን ሁሉ በፀሎት፣ በጉልበት፣ ጥሬ ዕቃ በማቅረብ፣ የበኩላችንን እንድንወጣ መንፈሣዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በእነዚህ ስልክ ደውሉ ፡ +251911 14 36 53 +251911 24 90 37 +251911 53 41 97 +251910 01 60 08 ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን !

ቤተ ክርስትያናቸው በአሕዛብ ሲቃጠል ለ34 ዓመታት ይህል በዋርካ ስር የምናየውን ስእለ አድህኖ ይዘው አምላካቸውን ሲያመልኩበት እስከዚች ሰዓት ቆይተዋል

Saturday, March 30, 2013

መፃጉዕ (የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት)


ምኩራብ (የዐቢይ ጾም ሦስተኛው ሳምንት)



ሦስተኛው ሰንበት ምኩራብ ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት በዚሁ ዕለት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ሰላሙ ድረስ በዕለተ ሰንበት «ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ»

«ምኩራብ» ማለትም ቀጥተኛ ፍችው ኮረብታ፣ ተራራ የሚያኸል ታላቅ ሕንጻ ማለት ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ የአይሁድ ቤተ ጸሎት ወይም ቤተመቅደስ ማለት ይሆናል፡፡ ዐቢይ ፍሬ ቃሉ ግን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድውያነ ሥጋን በትምህርቱ፣ ድውያነ ነፍስን በታምራቱ ሲፈውስ በምኩራብ እየተገኘ የፈጸመውን የማዳን ሥራ በኀሊና እያሳሰበ የሚያስተምር ሦስተኛ ሳምንት ነው፡፡ ዮሐ. 2:12

«ኢየሱስ በሰንበት ቀን ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ» እያለ ኢየሱስ በአይሁድ ምኩራብ ማስተማሩን እየጠቃቀሰና እያነሣሣ ስለሚዘምር ይህን ሰንበት ለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ እየገባ ለማስተማሩና በምኩራብ የሚሸጡ የሚለውጡ ነጋዴዎችን ለማስወጣቱ ቤተ መቅደሱን ለማስከበሩ መታሰቢያ ሆኖ ስለተሰጠ ነው፡፡ የዚህም በዓል ታሪክ ዝርዝር ሁኔታው በማቴዎስ ወንጌል ምዕ 21፡12-13 ተጠቅሷል፡፡
ቆላስ 2፡16-23 «እንግዲህ በመብል ወይ በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፣ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፡፡ ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፣ ባላየውም ያለፈቃድ እየገባ፣ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ፤ እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፣ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፣ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል፡፡ ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ት ምህር ት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፣ እንደሰው ሥርዓትና ት ምህር ት፡- አትያዝ አትቅመስ፣ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም ሁሉ እንደምትኖሩ ስለምን ትገዛላችሁ) እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና፡፡ ይህ እንደገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቈን ጥበብ ያለው ይመስላል፣ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም፡፡»

ያዕ 2፡14-26 « ወንድሞቼ ሆይ፣ እምነት አለኝ የሚል፣ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል) እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን) ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፣ ከእናንተ አንዱም በደህና ሂዱ፣ እሳት ሙቁ፣ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል) እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፡፡

ነገር ግን አንድ ሰው አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፣ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል፡፡ በእግዚአብሔር አንድ እንደሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል፡፡ አንተ ከንቱ ሰው፣ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን) አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን) እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፣ በሥራም እምነት እንደተፈጸመ ትመለከታለህን) መጽሐፍም አብርሃምም እግዚአብሔር አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፡፡ ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ፡፡ እንደዚሁም ጋለሞይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን) ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው፡፡»

የሐዋ.ሥራ 1ዐ፡1-9 « በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበር፡፡ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ፡፡ ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል፡- ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው እርሱም ትኩር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ ጌታ ሆይ ምንድር ነው) አለ፡፡ መልአኩም አለው፡- ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን ዐረገ፡፡ አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ፡፡ እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቁርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል፡፡ የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ ከሎሌዎቹ ሁለቱን፣ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፣ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው፡፡ እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፣ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ፡፡

መዝ 68፡9
እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ
ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ
ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡

የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና
የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና
ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፡፡

ዮሐ 2፡12-25 «ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀመዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፣ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ፡፡ የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ ወደ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፣ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ፡፡ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደተጻፈ አሰቡ፡፡ ስለዚህ አይሁድ መልሰው ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክ ት ታሳየናለህ) አሉት፡፡ ኢየሱስም መልሶ ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው ስለዚህ አይሁድ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፣ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን) አሉት፡፡ እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተመቅደስ ይል ነበር፡፡ ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ይህን እንደተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ፡፡

በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፣ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፣ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና፡፡»

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


Source : http://www.eotc-mkidusan.org/

Sunday, March 17, 2013

ቅድስት ( የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት )




«ቅድስት» ማለት የዘይቤ ፍችው « የተቀደሰች የተለየች » ማለት ነው፡፡ ምስጢራዊ መልእክቱ ግን የምስጢረ አድኅኖት ታላላቅ ሥራውን ለመጀመር መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ በገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ከቆመ ሳያርፍ፣ ከዘረጋ ሳያጥፍ የጾማት የአርብዓው ቀንና ሌሊት ልዩ የሆነችና ክብርት ጾም የምትጀመርበትን ሁለተኛ ሳምንት ከልብ ያሳስበናል፡፡ ማቴ. 4-2

ቅድሰት የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሰንበት ስያሜ ነው፡፡ ስያሜውም ከኢትዮያዊው የዜማ ሊቅ ከቅዱስ ያሬድ የተገኘ ነው፡፡ ከዚህ ሰንበት ዋዜማ ጀምሮ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ይዘመራል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ሰንበቱን ስለ ቅድስና ልጆቿን  ታስተምርበታለች ፡፡ በቅዳሴ ጊዜ የሚሰበከው ምስባክ የሚነበቡ መልዕክታት ፤የሐዋርያት ሥራ ወንጌል ስለ ቅድስት የሚያስተምሩ ናቸው፡፡

‹‹ቅዱስ›› ማለት ልዩ፤ክቡር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በባሕርዩ ቅዱስ ነው፡፡ ይህም ቅድስና ከማንም ያላገኘው የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ መጻሕፍትም የባሕርይ ቅድስናውን ተባብረው መስክረዋል፡፡ ባባሕርዩ ቅዱስ ስለሆነ ‹‹ቅዱስ፡ቅዱስ፡ቅዱስ›› እየተባለ ይመሰገናል፡፡( ኢሳ 61-34025 ራዕ 154 1ሳሙ22-3፡፡) እኛም ቅዱስ ልጁ በሥጋ ተገልጦ እንዳስተማረን በየዕለት ጸሎታችን ‹‹ስምህ ይቀደስ›› እንለዋለን፡፡ የቅድስና ምንጭ ቅድስናን የሚሰጥ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ ቅዱስ›› የሚለው ቃል ለሰዎች ፡ለመላእክት ለቦታ ፡ለዕቃ፡ ለዕለታት ቢቀጸልም ቅድስናቸው በባሕርይው ቅዱስ ከሆነው ከእግዚአብሔር የተገኘ ነው፡፡ይህም የጸጋ ቅድስና ይባላል፡፡

እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ በመልኩና በምሳሌው አክብሮ የፈጠረንን እኛም ቅዱሳን እንድንሆን ይፈለጋል፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁን›› ተብሎ ስለተጻፈ የጠራቸው ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ ›› ያለንም ይህንን ሲያስተምረን ነው፡፡ ከመፈጠራችን አስቀድሞ መጠን በሌለው ፍቅር የወደደን እግዚአብሔር ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣን ፤ለውርደት ሳይሆን ለክብር፤ለርኩሰት ሳይሆን ለቅድስና፤ለሞት ሳይሆን ለሕይወት ነው፡፡የመፈጠራችንም ዓላማ በፊቱ በፍጹም ምግባርና ሃማኖት በመመላለስ ከእርሱ ጋር እንድንኖር ነው፡፡ ብርሃን ከጨለማ፡ ጽድቅ ከኃጢአት፡ጋር ኅብረት የለውምና ከእርሱ ጋር ለዘላለም ነግሰን ለመኖር በቅድስና መኖር ይጠበቅብናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ እግዚአብሔር ለቅድስና እንጂ ለርኩሰት አልጠራንምና ›› ያለንም ለዚህ ነው፡፡/1ተሰ 4*7/  እግዚአብሔር እኛን የፈጠረበትን አላማ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች እንዲህ ገልጾላቸዋል ‹‹ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰማያዊ ሥፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ብሎ ካመሰገነ በኋላ ‹‹ ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳን ፡ንጹሐንና ያለነውር በፍቅር ያደርገን ዘንድ ለእርሱ መረጠን›› ኤፌ 13-4 አስቀድሞ ስለወደደንና ስላከበረንም ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ መልኩ የሚያስፈልገንን ሁሉ አዘጋጅቶ በእጆቹ ካበጀን በኋላ የሥነ ፍጥረት ዘውድ አድርጎ በገነት አኖረን ፡፡( ዘፍ 126 ፤መዝ 81)

የቀደመው አዳም አታድርግ የተባለውን በማድረጉ በንዝህላልነትና በስንፍና በከይሲ ዲያብሎስም ምክር ተዋረደ፡፡ በሞተ ሥጋ ላይም ሞተ ነፍስ ፤በርዕደተ መቃብር ላይ ርዕደተ ሲኦል ተፈረደበት፡ በባሕርዩ ሞት ገባበት፡ተዳደፈ፡፡ ክፉ ፍትወታት የሚያጠቁትና የሚያሸንፉት የዲያብሎስና የኃጢአት ባርያ ሆነ፡፡ በማይለወጥ ፍቅር የወደደን እግዚአብሔር ግን ጠፍተን እንድንቀር አልተወንም፡፡ በሰጠን ተስፋ፡በተቆጠረው ሱባኤና በተነገረው ትንቢት መሰረት ዘመኑ ሲደርስ በተዋህዶ ሰው ሆነ፤ የተዋረደ ሥጋችንን አከበረ፡፡ በከበረ ደሙ ዋጀን፤ከኃጢአታችን አጠበን፡፡ በእርሱ ምክንያት የእግዚአብሔር ልጆች ተባልን ፡፡ጌታችንና መድኃኒታችን  ሰው የሆነውና ለመዳናችን የሆነውን ዋጋ ሁሉ የከፈለው ለእኛ ያለውን ፍቅርና ለኃጢአት ያለውን  ጥላቻ ለእኛ ለማሳየት ነው፡፡ ‹‹ ነገር ግን የኃጢአትን ሥራ ይሽር ዘንድ ከእርሱ ጋር የተሰቀለውን አሮጌውን ሰውነታችን እንደሆነ ይህን እናውቃለን ›› የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ (ሮሜ 66)  እኛን ወደ ቀደመ ክብራችን ለመመለስ የተከፈለውም ዋጋ ታላቅ ከሆነው የጋብቻ ምስጢር ጋር በማያያዝ እንዲህ ገልፆታል ‹‹ ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው ቤተ ክርሰቲያን ራስዋ አዳኝዋም እንደሆነ ወንድ ለሴት ራስዋ ነውና ወንዶችም ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደዳት ራሱንም ስለእርስዋ ቤዛ አድርጎ እንደሰጠላት ሚስቶቻቸውን  ይውደዱ፡፡ በውኃ ጥምቀትና በቃሉ ይቀድሳትና ያነጻት ዘንድ የነጻችና የተቀደሰች ትሆን ዘንድ እንጂ በላይዋ እድፈት ወይም ርኩሰት እንዳይገኝባት ቤተ ክስቲያኑን ለእርሱ የከበረች ያደርጋት ዘንድ…›› ኤፌ 523-28
    ስለዚህ ጌታችን በደሙ ኃጢአታችንን እንደ ቸርነቱ ይቅር ብሎናል፡፡ኤፌ 17 ከእንግዲህ የራሳችን አይደለንም ፡፡ በሰውነታችንም ኃጢአትና ዐመፃን ልናደርግበት አይገባም ፡፡‹‹በዚህ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አታንግሷት፤ለምኞቱ እሺ አትበሉት፡፡ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሳ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጉ እንጂ ሰውነታችሁን ለኃጢአት የዐመፅ የጦር መሣሪያ አታድርጉት፤ ሰውነታችሁንም ለእግዚአብሔር የጽድቅ የጦር መሣሪያ አድርጉ››ተብለናል፡፡ (ሮሜ612-13)

የተወደዳችሁ ምዕመናን እግዚአብሔር ደስ ብሎት የሚቀበለውን ህይወት ለመኖር አንፈልጋለን ፡፡ ለመሆኑ ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ብንመላለስ ነው? መልሱን ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮቱ ከንቱ ነው፡፡ ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ወላጆች የሌሉአቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በችግራቸው መጠየቅ በዓለምም ከሚገኝ ርኩሰት ሰውነትን መጠበቅ ነው፡፡››በማለት ይመልስልናል( ያዕ 126-27)፡፡ በክርስቶስ ደም የተቀደሰና የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነውን ሰውነታችንን በዓለም ከሚገኝ ርኩሰት መጠበቅ የሰማያዊ ርስት ወራሾች ያደርገናል፡፡ በዓለም የሚገኘውን ርኩሰትም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የሥጋ ሥራ ›› በማለት ገልጾታል፡፡‹‹እርሱም ዝሙት ፣ርኩሰት፣መዳራት፣ጣዖት ማምለክ፣ሥራይ ማድረግ፣መጣላት፣ ኩራት፣የምንዝር ጌጥ ፣ቅናት፣ቁጣ ፣ጥርጥር፣ፉክክር፣ ምቀኝነት፣ መጋደል፣ ስካር ፣ይህንም የመሰለ ሁሉ ነው፡፡››እነዚህን የሚያደርጉ ሰዎችም ከመንግስተ እግዚአብሔር በአፍአ ወይም በውጭ እንደሚቀሩ ሲያስረዳ‹‹አስቀድሜ እንደነገርኋችሁ ይህን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግስት አያይም›› ብሏል ( ገላ519)

በሕይወታችን ሁሉ የምግባርና የሃይማኖት ፍሬ አፍርተን መገኘት ለቅድስና የጠራንን እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ነው፡፡እነዚህንም ነገሮች ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የመንፈስ ፍሬዎች ›› ብሏቸዋል፡፡ እነርሱም ‹‹ፍቅር፣ደስታ ፣ሰላም፣ትዕግስት፣ምጽዋት፣ቸርነት ፣እምነት ፣ገርነት ንጽሕና ››ናቸው፡፡ገላ 522 እግዚአብሔር ማደርያው ይሆን ዘንድ የመረጠውን ሰውነታችንን እርሱ የሚከብርበትን ሥራ ልናደርግበት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹በሕይወት የሚኖሩትም ስለ እነርሱ ቤዛ ሆኖ ለሞተውና ለተነሣውም እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው የሚኖሩ እንዳይሆኑ እርሱ ስለሁሉ ቤዛ ሆኖ ሞተ›› እንደተባለ  በሕይወታችን ሁሉ ፋቃዱን በመመርመርና በመፈጸም በቅድስና ልንኖር ይገባናል፡፡2ቆሮ 515

ቅድስናችን በኑሮአችን ሁሉ እንዲሆን ታዘናል (1ጴጥ115)፡፡ ስለዚህ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ፣በማኅበራዊ ኑራአችን ፣በምንበላው ምግብ ፣በምንለብሰው ልብስ ፣በንግግራችንና በመሳሰለው ሁሉ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኘውን በማድረግ እግዚአብሔርን በሚሞት ሥጋችን እናክብረው፡፡ ‹‹እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ የኃጢአትንም ጭንቀት ከእኛ አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግስት እንሩጥ፡፡ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን እንከተለው፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል ›› ተብሎ እንደተጻፈ ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ ተጋድሎ አድርገን ከኃጢአት ርቀት በቅድስና እንድንኖር ይገባናል(ዕብ 121) ሥጋዊ ምኞታችንንና መሻታችንን ሰቅለን አሮጌው ሰዋችንን አስወግደን ንስሐ ገብተን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለን በቅድስና እንድናኖር ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን፡፡


ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Source:  http://www.eotc-mkidusan.org/