Sunday, January 20, 2013

‹‹ቃና ዘገሊላ›› ምንድነው?



ቃና ዘገሊላ በቀጥታ ትርጉም የገሊላዋ ቃና ማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን አስተምህሮ በጥምቀት በዓል ማግስት(ጥር 12) ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል፡፡ ይህ በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ በድምቀት የሚከበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዳራ ያለው በዓል ነው፡፡ በዓሉ ቃና ዘገሊላ የሚል ስያሜ ያገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ሀገር ክፍል በምትሆን ቃና በተባለችው ቦታ በፈፀመው ተአምር መነሻነት ነው፡፡
የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ ወይም ታሪኩ የተፈፀመው የካቲት 23 ቀን ነው፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ብለው የየካቲቱን በዓል ወደ ጥር 12 አምጥተውታል፡፡ ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ለማስተሣሠር ለማስኬድ ነው፡፡ በመሆኑም የቃና ዘገሊላ በዓል ጥር 12 ቀን ይከበራል፡፡

በቃና ዘገሊላ ምን ተፈፀመ?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና በተደረገ ሠርግ ላይ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር ተገኝቶ ነበር፡፡ ‹‹ወሀለወት ህየ እሙ ለእግዚእ ኢየሱስ›› ‹‹የጌታ የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች›› እንዳለ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ (ዮሐ 2÷1) እመቤታችን ለሠርገኞቹ ዘመድ ነበረችና ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሰርጉ ላይ ታድማ ነበር፡፡ እናትን ጠርቶ ልጅን መተው ሥርዓት ስላልሆነ፤ በተጨማሪ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ከጌታ ጋር በሰርጉ ታድመዋል፡፡ ይህም መምህርን ጠርቶ ደቀ መዛሙርቱን መተው ሥርዓት ስላልሆነ (ተገቢ ስላልሆነ) ነው፡፡ የሠርጉ ሥነ-ሥርዓት በሠመረ ባማረ ሁኔታ እየተከናወነ ሳለ ድንገት የወይን ጠጅ አለቀ፡፡ አስተናባሪዎቹ በጭንቀት ባሕር ሰጥመው ምን እንደሚያደርጉ ግራ በገባቸው በጠበባቸው ጊዜ የችግር ጊዜ ደራሽ የኃዘን ጊዜ አፅናኝ የሆነችው የአምላክ እናት ድንግል ማርያም ቅዱስ ገብርኤል እንደተናገረ በፀጋ የተሞላች ናትና (ሉቃ 1÷28) ማንም ሳይነግራት የልቦናቸውን ጭንቀት አይታ፣ ጎዶሎአቸውን ተመልክታ ወደ ልጃ_ ወደ ወዳጃ_ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወር ብላ ‹‹ወይንኬ አልቦሙ›› ‹‹ወይን ጠጅ እኮ አልቆባቸዋል›› አለችው፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› ‹‹ጊዜዬ ገና አልደረሰም›› አላት፡፡ እመቤታችንም ለአገልጋዮቹ ‹‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ›› አለቻቸው፡፡ ጌታም በቦታው የነበሩ ስድስት ጋኖች ውኃ ሞልተው እንዲያመጡ አዘዛቸው፡፡ ውኃውንም ወደ ወይን ለውጦ ለሊቀ ምርፋቅ (ለአሳዳሪው) እንዲሠጡት አዘዘ፡፡ አሳዳሪውም ወደ ወይን የተለወጠውን ውኃ በቀመሰ ጊዜ አደነቀ፡፡ ከወዴት እንደመጣ ስላላወቀ ሙሽራውን ‹‹ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል ከሰከሩም በኋላ መናኛውን ያቀርባል አንተ ግን መልካሙን እስከ አሁን አቆይተሃል›› አለው፡፡ ወይኑም በሰው እጅ ያይደለ በሠማያዊው አባት የተዘጋጀ ስለነበር ጣፋጭ እና ልብን የሚያስደስት ነበር፡፡
‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?››
ይህንን የጌታችንን ንግግር ብዙዎች በዘመናችን ሲሣሣቱበት ይታያል ፡፡ ክብር ይግባውና አምላካችን ይህንን የተናገረው እናቱን ሊያቃልል ሽቶ አይደለም፡፡ ስለሆነም ከመጽሐፍ ቅዱስ አንፃር ይህን አረፍተ ነገር መመልከቱ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በተናጠል ስንመለከት ‹‹አንቺ ሴት›› ሴት የሚል ቃል የፆታ መጠሪያ ነውና በፆታዋ አክብሮ ሲጠራት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሔዋን ከአዳም በተፈጠረች ጊዜ አዳም እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር ‹‹ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል›› (ዘፍ 2÷23) በመሆኑም ጌታ አንቺ ሴት ማለቱ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ መንሣቱን ለማጠየቅ ነው፡፡ ‹‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› የሚለውን ዐረፍተ ነገር የንቀት ስለመሰለን ብቻ ‘ የዳቦ መልክ የያዘ ድንጋይ፤ ዳቦ ነው እንደማይባል’ የንቀት ንግግር ነው ልንል አይገባም፡፡ ጌታም እንዲህ ሲል ውኃውን ወይን አድርግላቸው ብትይኝ አላደርግም እልሽ ዘንድ ከአንቺ ጋር ምን ፀብ አለኝ ማለቱ ነው፡፡ ይህ ንግግር በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ተጽፎ እንደሚገኘው በዕብራውያን ዘንድ የተለመደ የአነጋገር ዘይቤ ነው፡፡ለአብነት ይሆን ዘንድ ጥቂት ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት፡-
የሰራፕታዋ ሴት በ 1ነገ 17÷18 ላይ እንደምናገኘው ልጇ በሞተባት ጊዜ ኤልያስን በሐዘን በለቅሶ እንዲህ ብላ ነበር ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ?›› ትወልጃለሽ ብለህ የወለድኩት ልጅ ምን በድዬህ ምንስ አስከፍቼህ ሞተብኝ? ስትል ነው እንጂ አባባሏ የንቀት ወይም የማቃለል አይደለም፡፡
በጌርጌሴኖን አንድ አጋንንት ያደረበት ሰው ወደ ጌታችን ቀርቦ ‹‹የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ?›› አለው፡፡ እውነት ይህ ቃል የንቀት ይመስላልን? የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ብሎ አምላክነቱን እየመሰከረ ሊያቃልለው ይችላልን? ደግሞስ ላለመጥፋት ፍፁም የሚፈልግ ሰው ሊያድነው ሥልጣን ያለውን ሊንቅ ይችላልን? አይችልም፡፡ ይህ ቃል የሚያመለክተው ምን አጠፋሁ ስለምን ልታጠፋኝ ወደድክ በማለት መፍራት መራዱን ነው፡፡ (ሉቃ 8÷28-29)
ስለሆነም ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› የሚለው የንቀት አለመሆኑን ከሁለቱ ጥቅሶች መረዳት እንችላለን፡፡ እመቤታችን እና ጌታ በንግግር አልተቃረኑም ንግግራቸው የፍቅር ነበር፡፡ ንግግራቸው የመግባባት ስለነበር ነው ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› ካላት በኋላ ዘወር ብላ አገልጋዮቹን የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ ያለችው፡፡
‹‹ጊዜዬ አልደረሰም››
ጌታ ይህን ቃል የተናገረው ስለ ብዙ ምክንያቶች ነው፡፡ ጊዜዬ አልደረሰም ማለቱ፡-
እግዚአብሔር ነገሮችን የሚያከናውንበት የራሱ ጊዜ አለው፡፡ በመሆኑም ይህን ተአምር የምፈፅምበት ጊዜዬ አልደረሰም ሲል ነው፡፡
ጋኖቹ ውስጥ የቀረ ወይን ስለነበረ ባለው ላይ አበርክቶ እንጂ ውኃውን ወደ ወይን አልለወጠውም እንዳይሉ ወይኑ ከጋኑ ተንጠፍጥፎ እስኪያልቅ ድረስ ጊዜዬ አልደረሰም አለ፡፡
ይሁዳ ከሠርግ ቤት ወጣ ብሎ ነበርና ወደ ሠርግ ቤቱ እሰኪመለስ ጊዜዬ አልደረሰም አለ፡፡ ይሁዳ በቃና የገለጠውን ምስጢር ለእኔ ስላላሣየኝ ተከፍቼበት ከተአምራቱ ቢያጎድለኝ በሞቱ ገባሁበት፤ ሸጥኩት እንዳይል ምክንያት ለማሳጣት እንዲህ አድርጓል፡፡
እውነተኛ የሕይወት ወይን የሆነውን ደሜን የምሠጥበት ጊዜ ገና ነው ሲል፡፡
የድንግል ማርያም አማላጅነት በገሊላ ቃና
ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በሠርግ ቤት ሣለ የወይኑን ማለቅ የማይመለከት ሆኖ አይደለም፡፡ ነገር ግን የእናቱን የድንግል ማርያምን አማላጅነት ሊገልጥ ስለወይኑ ማለቅ እስክትነግረው ድረስ አንዳች ነገር አላደረገም፡፡ ኋላ ግን የጭንቀት አማላጅ ድንግል ማርያም ስለ ወይኑ አሰበች ልጇ ወዳጇን ለመነች፡፡ እርሱም የእናቱን ልመና ተቀብሎ ተአምራቱን ፈፀመ፡፡ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሣይነግሯት በልብ ያለውን የምታውቅ የምትመረምር እናት ናትና የሠርጉ አስተናባሪዎች ይሄ ጎደለ ሣይሏት የልቦናቸውን ሐዘን ተመልክታ ከልጇ ከወዳጇ አማልዳ የጎደላቸውን ሞልታለች፡፡ ያስጨነቃቸውንም አርቃለች፡፡ በችግራቸው ደርሳላቸዋለች፡፡ ታዲያ ሳይነግሯት የልቡናን አይታ ከማለደች ስሟን ጠርተው ለሚለምኗትም እንዴት አብልጣ አታማልድ?
ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤቷን በረከቷን ያሳድርብን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ ፦ በአፍሪካ ኅብረት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ሰንበት ት/ቤት መማማሪያ ገ

Friday, January 18, 2013

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ።




ጥምቀት በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋኒያ በግእዝ አስተርዮ በአማርኛ መገለጥ ይባላል፡፡ ቃሉ በቀጥታ ሲተረጎም በውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት፣ መነከር፣ መዘፈቅ፣ መጥለቅ ማለት ነው፡፡ ጥምቀት ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን (ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቁርባን፣ ምሥጢረ ንስሐ፣ ምሥጢረ ክህነት፣ ምሥጢረ ተክሊል፣ ምሥጢረ ቀንዲል) አንዱና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ በዮሐ. 3፥5 ላይ ‹‹እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡›› ብሎ እንደተናገረው ከውኃና ከመንፈስ ተወልደን የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት ኃጢአታችን የሚደመሰስበት ድኅነትን የምናገኝበት ዐቢይ ምሥጢር ነው፡፡ ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ አምኖ ለሚፈጽመው ሰው ሁሉ ለኃጢአት መደምሰሻ ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት ለመቀበልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የተሰጠ ልዩ የሕይወት መንገድ ነው፡፡
 የጥምቀት አመጣጥ
የምሥጢረ ጥምቀት መስራች ራሱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ነገር ግን ከጌታችን ጥምቀት በፊት አይሁድ ለመንጻትና ለኃጢአት ሥርየት (ይቅርታ) የሚጠመቁት ጥምቀት ነበራቸው፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር በረድኤት የሚገለጥባቸው የተቀደሱ ዕለታትና ቦታዎች ሁሉ ሰውነትንና ልብስን ማጠብ የእግዚአብሔር ቤት ማገልገያ የሆኑ ዕቃዎችን ሁሉ ማጠብ ማንጻት ሥርዓትና ልማድ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርም ፈቃድ ያለበት አሠራር ነበር፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት ከመቅረባቸውና ለተቀደሰው አገልግሎት ከመግባታቸው አስቀድመው እግሮቻቸውንና እጆቻቸውን የመታጠብ ግዴታም ነበራቸው፡፡ ሰውነታቸውን ከአፍአዊ (ከውጫዊ) እድፍ በማጠብና ንጹሕ በማድረግ በባሕርይ ንጹሕና ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት ውስጣዊ ሕይወትን ንጹሕ አድርጎ የመቅረብን ሥርዓትና ምሥጢር የሚያመለክት ልማድ ነበር፡፡
‹‹አሮንንና ልጆቹን ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ታቀርባቸዋለህ፤ በውኃም ታጥባቸዋለህ›› /ዘፀ. 29፥4/
‹‹ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፣ በውኃም አጠባቸው፡፡›› /ዘሌ. 8፥6/
በብሉይ ኪዳን ዘመን የጥምቀት ምሳሌዎች
  1. አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከጼዴቅ መሄዱ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም የምእመናን መልከጼዴቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ናቸው፡፡ /ዘፍ. 14፥17/
  2. ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል፡፡ ይህም ምእመናን ተጠምቀው ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የመፈወሳቸው ምሳሌ ነው፡፡
  3. ንዕማን ሶርያዊ ተጠምቆ ከለምጽ ድኗል፡፡ 2ነገ. 5፥14 ይኸውም ምእመናን ተጠምቀው ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የመዳናቸው ምሳሌ ነው፡፡
  4. የኖኅ መርከብ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ. 6፥13 ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑባትን መርከብ ሲሠራ በኖኅ ዘመን የእግዚአብሔር ትዕግሥት በዘገየ ጊዜ ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ሰበከላቸው፡፡ አሁንም እኛን በዚያው አምሳል በጥምቀት ያድነናል ሥጋን ከዕድፍ በመታጠብ አይደለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመነሣቱ በእግዚአብሔር እንድናምን መልካም ግብርን ያስተምረን ዘንድ ነው እንጂ፡፡›› /1ጴጥ. 3፥20/
  5. እስራኤል በደመና ተጋርደው ቀይ ባሕርን መሻገራቸው የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ /ዘፀ. 14፥15/ ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አባቶቻችን ሁሉ ደመና እንደ ጋረዳቸው ሁሉም በባሕር መካከል አልፈው እንደ ሄዱ ልታውቁ እወዳለሁ፡፡ ሁሉንም ሙሴ በደመናና በባሕር አጠመቃቸው›› /1ቆሮ. 10፥1/
  6. ለአብርሃም ሕግ ሆኖ የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም ከአረጀ በኋላ ቢገረዝም ልጆቹ ግን በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ እግዚአብሔር አዞ ነበር /ዘፍ. 17፥9/ ‹‹በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ፡፡ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል፡፡›› /ቈላ. 2፥11/
ጌታችን ለምን ተጠመቀ?
1. ሚሥጢርን ለመግለጥ፡- ጌታችን በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ ሚስጢረ ሥላሴ ግልፅ ሆኗል፡፡ አብ በደመና የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው በማለቱ አብ የወልድ አባት መሆኑ ታወቀ፡፡ መንፈስ ቅዱስም የባሕርይ ሕይወቱ መሆኑን ሲያስረዳ በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ተቀመጠ ወልድም በተለየ አካሉ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ታየ፡፡ ስለዚህ ምሥጢርን ለመግለጥ ስንል የአንድነት የሦስትነት ምስጢር በጐላ ሁኔታ እንዲታወቅ ተጠመቀ ማለት ነው፡፡ /ማቴ. 3፥16/
2. ትንቢቱን ለመፈፀም፡- በመዝ 46/77/16 ላይ አቤቱ ውሆች አዩህ፣ ውሆችም አይተውህ ፈሩ ጥልቆች ተነዋወጡ ውሆችም ጮኹ፡፡ ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረውን ትንቢት ለመፈፀም ተጠመቀ፡፡
3. አርአያ ሊሆነን፡- ተጠምቆ እንድንጠመቅ አደረገን ሥርዓትን ሠራልን ቀድሞ በአርአያውና በአምሳሉ እንደፈጠረን አሁንም አርአያ ምሳሌ ሆነን፡፡ ለዚህም ነው ምሳሌን ከእኔ ተማሩ ያለን፡፡ /ማቴ 1129/ ለትምህርት ለአርአያ /ዮሐ. 13፥1-17/
4. የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ፡- አዳምና ሔዋን ፍዳው በፀናባቸው መከራው በበዛባቸው ጊዜ የሚያቃልልላቸው መስሏቸው ዲያብሎሰ ስመ ግብርናችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ ባላቸው ጊዜ አዳም ገብሩ ለዲያቢሎስ (አዳም የዲያብሎስ የወንድ አገልጋይ) ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ (ሔዋን የዲያብሎስ ሴት አገልጋይ) ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ዲያብሎስም ይህንን ደብዳቤ አንዱን በሲኦል አንዱን በዮርዳኖስ አስቀመጠው፡፡ በዮርዳኖስ ያስቀመጠውን ጌታችን ሲጠመቅ እንደሰውነቱ ረግጦ ደምስሶታል፡፡ ይህንን ጽሕፈት ለመደምሰስ ነው ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተፃፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፡፡ ያለው ቆላ 214
ጌታችን መች ተጠመቀ?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በ5531 ዓመተ ዓለም ዘመነ ሉቃስ ማክሰኞ ጥር 11 ቀን ከሌሊቱ በ10ኛው ሰዓት ነበር፡፡ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 19 በተጠመቀም ጊዜ ዕድሜው 30 ዓመት ከ13 ቀን ነበር፡፡ /ሉቃ. 3፥23/
ጌታችን ስለምን በ30 ዓመት ተጠመቀ?
በብሉይ ኪዳን ሥርዓትና ልማድ ካህናት ለቤተ እግዚአብሔር ተልእኮ እና መንፈሳውያን አገልግሎቶች ከ30 ዓመት ዕድሜ በፊት አደባባይ አይወጡም ነበር፡፡ እጅግ አስፈላጊ እንኳ ቢሆን ከ20 እና 25 ዓመት አስቀድሞ ለአገልግሎት መሰየም ልማድ አልነበረም፡፡ የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች በዕድሜና በዕውቀት የበሰሉ፣ በጠባይና በሥራ ልምድ የተፈተኑ ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት በተገልጋዩ ሕዝብ ዘንድ የተመሰከረላቸው መሆን ነበረባቸው፡፡ /ዘፀ. 4፥3፤1ዜና መዋ. 23፥24፤ 1ጢሞ. 3፥6-10/ ያንን ሥርዓት ለመፈጸም ጌታችን የተጠመቀውና ለትምህርተ ወንጌል የተገለጠው በ30 ዓመቱ ነበር፡፡ ዮሐንስ መጥምቅም የጌታን መምጣት ለማወጅ በዮርዳኖስ ይሁዳ ምድረ በዳዎች ወጥቶ የታየው ከ30 ዓመት ዕድሜው በኋላ ነው፡፡ ሌላው ዐቢይ ምክንያት የሰው ሁሉ መጀመሪያ አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ በ40ኛ ቀን ተሰጥቶት ኋላም በኃጢአት ምክንያት ያስወሰደውን ልጅነት ለማስመለስ ነው፡፡ ክርስቶስ የተጠመቀው ክብር ሽቶ ሳይሆን የአብ የባሕርይ ልጅነቱን (የባሕርይ አምላክነቱን) ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ለማስመስከር፣ ውኃውን ለመቀደስ፣ የአዳምን ልጆች የእዳ ደብዳቤ ለመደምሰስና በስህተት የጠፋውን የልጅነት ክብር ለመመለስ ነው፡፡ ጌታ ተጠምቆ ከውኃው ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ በማረፍ አብ በደመና ‹‹ይህ ልጄ ነው›› ብሎ ሲመሰክርለት ምሥጢረ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በጉልህ ተረጋግጧል፡፡ /ማቴ. 3፥16/


ጌታችን በዮሐንስ እጅ ለምን ተጠመቀ?
ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ሲሆን በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ በፍጹም ትሕትና ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ ይህንንም ያደረገልን አብነት ሊሆነን ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ቅዱስ ዮሐንስን ‹‹መጥተህ አጥምቀኝ ›› ብሎት ቢሆን ኖሮ ነገ ነገሥታቱና መኳንንቱ ካህናቱን መጥታችሁ አጥምቁን ባሉ ነበር ስለዚህ እንዲህ እንዳይሆን ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ጌታ ስሆን በባርያዬ እጅ እንደተጠመቅሁ እናንተም ወደ ቤተክርስቲያን ሄዳችሁ በካህናት እጅ ተጠመቁ›› ሲል ነው፡፡
ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው ልጅነትን የምታሰጥ ጥምቀትን ባርኮ ቀድሶ ሊሰጠን እንጂ ክብር እንዲሆነው አይደለም፡፡ ምክንያቱም፡- እርሱ እከብር አይል ክቡር እጸድቅ አይል ጻድቅ ነውና፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን በማን ስም አጠመቀው?
ጌታችን ዮሐንስን አጥምቀኝ ባለው ጊዜ ‹‹ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ አንተን በማን ስም ላጥምቅህ? በአብ ስም እንዳላጠምቅህ አብ አባትህ ባንተ ሕልው ነው በወልድ ስም እንዳላጠምቅህ ወልድ አንተ ነህ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዳላጠምቅህ መንፈስ ቅዱስ ሕይወትህ ባንተ ሕልው ነው ታዲያ በማን ስም ላጥምቅህ?›› ብሎ ቢጠይቀው ጌታም ‹‹እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት አንተ የዓለም ካህን ብርሃንን የምትገልጥ የአብ የባሕርይ ልጅ ሆይ ይቅር በለኝ›› ብለህ አጥምቀኝ አለው፡፡
ዮሐንስ ጌታን ሲያጠምቀው እጁን ለምን አልጫነበትም?
-    ዮሐንስ በጥምቀት አከበረው /ልዕልና ሰጠው/ እንዳይባል፡፡
-    መለኮትን በእጅ መንካት ስለማይቻል
ጌታችን ጥምቀቱን ለምን በዮርዳኖስ አደረገው?
በኢየሩሳሌም አካባቢ ብዙ ወንዞች ኩሬዎችና ሐይቆች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ጌታ ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለዚሁ አስቀድሞ የተነገረውን ትንቢት መፈጸሙን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ‹‹ባሕር አይታ ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ›› /መዝ. 113፥3/ ከዚህም ጋር ከላይ ምንጩ አንድ የሆነው ዮርዳኖስ ዝቅ ብሎ በደሴት ተከፍሎ እንደገና እንደሚገናኝ በግዝረት በቁልፈት (በመገዘርና ባለመገዘር) ተለያይተው የነበሩ ሕዝብና አሕዛብ መላው የአዳም ልጆች በጌታችን ጥምቀት አንድ መሆናቸውን የሚገልጽ ትርጉም አለው፡፡ እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምደረ ርስት ገብተዋል፡፡ ያመኑ የተጠመቁ ምዕመናንም በጥምቀት ገነት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡ ሌላው በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ይደመስስልን ዘንድ /ቈላ. 2፥14/
ጌታችን ለምን በሌሊት ተጠመቀ?
በኃጢአት ጨለማ ስለነበረ ሕዝብ የጽድቅ ብርሃን እንዲወጣለትና በጨለማ የሚመስል ኦሪት ይኖር ስለነበረ ለሕዝብ ብርሃን የሆነ ወንጌል መገለጡን ለማሳየት ነው፡፡ ኢሳ. 9፥2
-    አንድም ጌታ ልደቱ፣ ጥምቀቱ፣ ትንሣኤው እንዲሁም ምጽአቱ በሌሊት ነው፡፡ ይኽም የሆነበት ምክንያት፡- ሌሊቱን ተከትሎ የሚመጣው ብርሃን በመሆኑ ከሞት ወደ ሕይወት ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሲኦል ወደ ገነት የመሸጋገራችን ምሳሌ ነው፡፡
-    አንድም መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል የሚወርድ ነውና በጌታ ላይ የወረደው ርግብ እንጂ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ባሉ ነበር፡፡ በሌሊት ርግብ የለም ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ይታወቅ ዘንድ፡፡
መንፈስ ቅዱስ ለምን ጌታ ከውኃ ከወጣ በኋላ ወረደ?
ሀ. ዮሐንስን ያከብሩት ነበርና መንፈስ ቅዱስ የወረደው ለዮሐንስ እንጂ ለጌታ አይደለም ይሉ ነበርና ምክንያቱን ጌታ ውኃ ውስጥ እያለ ከዮሐንስ አልተለየም ነበርና፡፡
ለ. ውኃን የሚባርክ መልአክ እንዳለ ያውቁ ነበርና ውኃውን ለመባረክ አንጂ ለጌታ አይደለም እንዳይባል፡፡
ሐ. ማረፊያ ያጣች ርግብ በባሕር ስትበር አረፈችበት ባሉ ነበርና ሐሳባቸውን በሙሉ ያጠፋ ዘንድ ከውኃ ውስጥ ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወረደ፡፡
 ወስብሐት ለእግዚአብሔር