Friday, April 26, 2013

ሆሣዕና


ሆሣዕና እና ምሳሌነቱ
ማቴ 21፡1-10


ሆሣዕና ማለት መድሃኒት ማለት ነው፡፡
ደብረ ዘይት ወይራ የበዛበት ተራራ ነው፡፡
ቤተ ሳጌ የድሆች መንደር ናት፡- ጌታ የድሆች መንደር ወደደ፡፡እኛ ድሆቹን ባለ ፀጋ ሊያደርገን ስለኛ ብሎ ራሱን ድሃ ያደረገ አምላክ ነውና፡፡
ቤተ ሳጌ ለእየሩሳሌም በጣም ቅርብ ናት፡፡እኛም ለቤተ ክርስትያን ቅርብ መሆን አለብን፡፡
እየሩ ሳሌም ቤተ ክርስትያን ናት እንቅረባት 
እየሩ ሳሌም እመቤታችን ናት እንቅረባት
ጌታ ቤተሳጌ በደረሰ ጊዜ የተመሳቀለ መንገድ ቁሞ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱ ላከ
*ሁሩ ሃገረ ቅድመክሙ* ወደ ፊታችሁ ላለው ሃገር ሂዱ ወደ መንደሪቱ ግቡ አላቸው፡፡ 

በተመሳቀለ ቦታ መቆሙ፡- ወደ ፊት በመስቀል ላይ እሰቀላለሁ ሲል ነው፡፡
ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ሲልካቸው በፊታችሁ ላለው ሃገር ሂዱ ያን ጊዜ አህያ ከውርንጭላዋ ጋር ታስራ ታገኛላችሁ ፈታችሁ አምጡልኝ አላቸው፡፡ 

ጌታችን ብዙ ያልታሰሩ አህዮች እያሉ ለምን የታሰሩትን መረጠ?

አህዮቹ የታሰሩት ሌባ ሰርቆ ነው ያሰራቸው፡፡ ወንበዴ ሰርቆ ነው ያሰራቸው 
አህዮቹ ለጌታ ውለታ ሰርተዋል፡፡ ጌታ ሲወለድ አሙቀውታልና፡፡ ለጌታ ውለታ ልንመልስ ያልቻልነው እኛ ሰዎች ብቻ ነን፡፡

የታሰሩት እዲፈቱ የመረጠበት ሚስጥር

እኔ ከሃጥአታችሁ ልፈታችሁ የመጣሁ ነኝ ሲል ነው፡፡
ወንበዴው አህዮቹን ሰርቆ በመንደር እንዳሰራቸው ዲያብሎስም ለሰው ልጅ በሃጥአት ሰንሰለት ከሲኦል መንደር አስራቸው ነበርና፡፡
ሃዋርያቱ ሲልካቸው ምን ታደርጋላችሁ የሚላችሁ ሰው ቢኖር ጌታቸው ይሻቸዋል በልዋቸው አላቸው፡፡ የፈጠራቸው እሱ ነውና፡፡ 

ከአህያዋ ጀርባ ሃዋርያት ልብሳቸው አነጠፉለት ለምን?

ለምንስ ኮርቻ አላደረጉለትም? ለምንስ ልብሳቸው መረጡ? 
ለስላሳ ህግ የሰራህልን አንተ አባት ነህ ሲሉ ነው
ለስላሳ ህግ የተባለው ወንጌል ነው
ወንጌል ፍቅር ናት የሚረግማችሁ መርቁ ትላለችና፡፡
ልብስ የሰውነት ነውር ይሸፍናል፡፡ ነውረ ሃጥአታችን የምትሸፍንልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡ እሱ ልብሳችን ነውና፡፡ ነውራችን የሚሸፍንልን እሱ ነውና፡፡
ችግሩ ግን ነውረ ሃጥአታችን የሚሸፍንልን ልብስ እርሱ መሆኑን አለማወቃችን ነው፡፡
አብሮን እንዳለ አለማስተዋላችን ነው፡፡ 
ስለዚ እደ ሃዋርያት ነውረ ሃጥአታችንን አስቀድመህም የሸፈንክልን ዛሬም የምትሸፍንልን ወደፊትም የምትሸፍንልን አምላክ አንተ ነህ ልንለው ይገባል፡፡

ጌታችን በሁለቱ አህያዎች በጥበብ ተቀመጠ፡- በሰው የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ግን የሚቻል መሆኑ ጥበበኛ አባት ሁሉን የሚችል አባት መሆኑ የሚገልጽ ነው፡፡ አንድም ወንጌልን ኦሪትና ሃዲስን ሁለቱ አስታርቆ አስማምቶ አንዱን አንዱን እየመገበ የሚሄድ መሆኑ የሚያመለክት ነው፡፡

ጌታ ለምን በፈረስ ላይ አልተቀመጠም?

ትንቢትና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡ ት.ዘካ9፡9 ፃዲቅ የባህሪ አምላክ የዋህ ሃዳጊ በቀል ንጉስሽ በአህያ በወርንጭላዋ ተቀምጦ ይመጣል ብላችሁ ለጽዮን ልጅ ንገርዋት ብለዋልና፡፡

ፈረስ
• ተንኮለኛ ናት ለጠላትዋም አውድቃ ረግጣ ትገድላለች
• ረጋ ብላ መሄድ አትችልም ትቸኩላለች
• ልትወጣባት ስትልም ታስቸግራለች አትመችም ተነጣጥረህ ነው የምትወጣባት 
• ጌታ የወደደውና በትንቢቱም እደተገለጸው አህያን መረጠ፡፡

በአህያ መቀመጡ
• ትህትናን ለማስተማር
• የሰላም ዘመን ነው ሲል 
• ለፈለጉኝ ሁሉ የቅርብ አምላክ ነኝ ሲል በንጽህና በየዋህነት ለሚኖሩ መእመናን አድሬባቸው እኖራለሁ ሲል፡፡
• አህያዎች ትሁታን ናቸው ረጋ ብለው ነው የሚሄዱት፤በቀላሉ ትወጣበታለህ፤በቀላሉ ትይዘዋለህ፤እንደፈለክም ታዝዋለህ፤እኛ በትእቢት ተይዘን ነው እንጂ በየዋህነት ብንመላለስ እሱ ያድርብን ነበር፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ማደርያ ነንና፡፡

ትልቅዋ አህያ የኦሪት ምሳሌ ነው
1. ትልቅዋ አህያ ሸክም የለመደች ናት ህገ ኦሪትም የተለመደች ህግ ናትና፡፡
2. የእስራኤል ምሳሌ ነው፡-ትልቅዋ አህያ ሸክም እንደለመደች ሁሉ እስራኤልም ህግ ለመፈጸም በህግ ለመራመድ የለመዱ ናቸው፡፡
3. የአዳም ምሳሌ ነው፡- አዳም ሸክም የበዛበት ነበርና 

ውርጭላዋ
1. በህገ ወንጌል ትመሰላለች፡-ምክንያቱም ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰረታት የሰራት አዲስዋ ህግ ናትና፡፡
2. በአህዛብ ትመሰላለች፡-ትንሽዋ አህያ ሸክም የለመደች አይደለችም እንዲሁም አህዛብም ህግህን የመቀበል የለመደ አይደሉም፡፡ ለህግህ አዲስ ናቸውና፡፡
3. የእመቤታችን ምሳሌ ናት፡- የዓለም ሸክም አቅልላለችና በእመቤታችን ትመሰለላለች፡፡ እመቤታችን ድህነተ ምክንያታችን ጌታን የተሸከመች ንጽህት እንከን የሌላት እናት ናትና፡፡


ህዝቡም ልብሳቸው እያወለቁ በጎዳና አነጡፉለት ለምን?

እንኮን አንተ የተቀመጥክባት አህያም ክብር ይገባታል ብለው ነው፡፡ 
እስራኤላውያን ጌታ የተቀመጠባት አህያ አከበሩ፡፡ ይህ ትውልድ ግን ጌታ የተቀመጠባት እመቤታችን ማክበር ተሳናቸው፡፡
ልብሳቸው ማንጠፋቸው፡- ለክብሩ መግለጫ ነው፡፡

ሌሎችም ቅጠል አነጠፉለት፡ ሶስት አይነት ቅጠል አነጠፉለት
ዝንባባ፤የቴመር ዛፍ፤የወይራ ዛፍ አነጠፉለት፡፡


ዝንባባ
1. ዝንባባ፡- ይስሃቅ በተወለደ ጊዜ ደስ ብሎት አብርሃምን ዝንባባ ይዞ እግዚአብሔር አመስግነዋል፡፡
2. ዝንባባ ደርቆ እንደገና ሂወት ይዘራል፡- የደረቀ ሂወታችን የምታለመልም አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
3. ዝንባባ የሰላም ምልክት ነው፡- የሰላም አምላክ ነህ ሲሉ ነው
4. ዝንባባ የደስታ መግለጫ ነው፡- አንተ ደስ የምታሰኝ ሃዘናችንም የምታርቅልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
5. ዝንባባ እሾሃማ ነው፡- አንተ ህያው አሸናፊ አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
6. ዝንባባ እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል እንጂ፡፡ ጌታም አንተ ባህሪህን የማይመረመር ነው ሲሉ ነው፡፡

የቴምር ዛፍ፡-
1. የቴምር ፍሬ መራራ ጣፋጭም ነው፡- በሃጥአት የመረረውን ሂወታችን የምታጣፍጥልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
2. የቴምር ዛፍ ከፍ ያለ ነው፡-አንተ አምላካችን ልዑለ ባህሪ ነህ፡፡ ከፍ ከፍ ያልክ አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
3. የቴምር ፍሬ በውስጡ ያለውን አንድ ነው፡-አንድ አካል አንድ ባህሪ ነህ ሲሉ ነው፡፡
4. የቴምር ፍሬው በእሾህ የተከበበ ነው፡- ይህም የአንተ ባህሪ የማይመረመር በእሳት የተከበበ ነው ሲሉ ነው፡፡ 


የወይራ ቅርንጫፍ ዛፍ
1. የወይራ ቅጠል ከእንጨት ሁሉ ጽኑ ነው፡፡ አንተም ጽኑ ሃያል አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
2. ወይራ ለመብራት ያገለግላል ዜት ያወጣል፡- ከወይራ የሚገኝ ዘይት ጨለማን አሸንፎ ብርሃን እንደሚሰጥ ሁሉ አንተም ጨለማ ሂወታችን የምታስወግድልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
3. በኦሪት ጊዜ ከወይራ የተገኘ ዘይት ለመስዋእትነት ይቀርብ ነበር፡፡ አንተም እንደ ዘይቱ ለመስዋእት የምትቀርብ አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡ በመስቀል ላይ መስዋእት ሁነዋልና፡፡


ሆሣዕና በእጃችን እደ ቀለበት ማሰራችን የምን ምሳሌ ነው?

1. ጌታ ለአዳም የሰጠው ቃል ኪዳን ለማስታወስ፡-ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድነሃለሁ ያለውን የተስፋ ቃል ለማስታወስ፡፡
2. ጌታ ለእመቤታችን የገባላትን ቃል ኪዳን ተምሳሌት ነው
3. ጌታ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ቃል ኪዳን ተምሳሌት ነው
4. ጌታ ለአዳም ከሰይጣን ግዛት ነጻ እንዳወጣው ሁሉ እኛም ከሰይጣን ግዛት ከመከራ ስጋ ከመከራ ነፍስ ከክፋት ከሃጥአት አውጣን ማረን ለንስሃ ሞት አብቃን ከቤትህ አትለየን እንደ ቸርነትህ ይቅር በላን ስንል ከጌታ ደግመን ላናጠፋ ቃል የምንገባበት ነው፡፡
ስለዚ እንደ ታሰሩ አህዮች መፈታት አለብን፡፡ ሁላችን ታስረናልና ቤተ ክርስትያን በመሄድ እንድንፈታ እናድርግ፡፡ የታሰሩት ሁሉ በካህናት አባቶቻችን አማካኝነት እዲፈቱ ልናድርግ ይገባናል፡፡ ለምን ቢባል አምላካችን ይፈልገናል አባታችን አማላካን ንጉሳችን ይፈልገናል፡፡ ጌታ ጸጋውን አብዝቶ ለዘላለሙ ከቤቱ አይለየን የነጻነት አባት ካለን ሱስና ልማድ ሁሉ ነጻ አድርጎ ለሱ እንድንገዛ እርሱ ይርዳን አሜን መልካም በዓል፡፡

ኒቆዲሞስ



ክርስቲያን ፊደል- ኒቆዲሞ
ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ የምስራቹን ቃል ሲያውጅ እስራኤላውያን የተቀበሉት በተደበላለቀ ስሜት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ሕዝቡ ለብዙ ዘመናት በባርነት ሲገዛ ስለነበር ከሮማውያን ቅኝ ግዛት ነጻ የሚያወጣቸው መሲህ ይፈልጋሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ ለብዙ ዘመናት በባርነት ቀንበር ስለደከመ ተስፋ በመቁረጥ ተዳክሞ ነበር፡፡ መሲህ ቢመጣ እንኳ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት ጦር ይዞ ሰራዊት አስከትሎ ነው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው ክርስቶስን መሲህ ነኝ ብሎ ሲመጣ ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጦር ሳይዝ ሰራዊት ሳያስከትል እንዲሁ ባዶ እጁን አርነት ላወጣችሁ መጥቻለሁ እያለ ደጋግሞ ተናግሯልና ነው፡፡ ምንም እንኳ አብዛኛው እስራኤላዊ የክርስቶስን መሲህነት ቢጠራጠርና ባይቀበለውም፣ በፍጹም እምነት እስከ መጨረሻው የተከተሉትም ነበሩ፡፡ ለዚህም ትልቅ ማሳያ የሚሆነን ከፈሪሳውያን ወገን የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አይሁዳዊ ነው፡፡ቅድስት ቤተክርስቲያንም ይህን ታላቅ ሰው ለማዘከር የዐቢይን ጾም ሰባተኛ እሁድ በእርሱ ስም ሰይማ ታከብረዋለች ፡፡ ተከታዮቿ ምዕመናንም የእርሱን አሰረ ፍኖት እንዲከተሉ ትመክራለች ታስተምራለችም፡፡
ኒቆዲሞስ ማነው?

፩. ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ነው ዮሐ 3-1
የእስራኤላዊያን ለብዙ ዘመን በባርነት መኖር የሕዝቡን የአኗኗር ሁኔታ ቀይሮታል፡፡በግዞት ጊዜ ከአሕዛብ የቀሰሟቸው አጉል ትምህርቶች በእምነትም በአስተሳሰብም እጅግ እንዲለያዩና እንዲራራቁ ምክንያት ሆኗል፡፡ አይሁዳዊ ሳምራዊ፤ ከአይሁድም ሰዱቃዊ ፣ ፈሪሳዊ ፣ ጸሐፍት ፣ ኤሴያዊ ብለው እንዲከፋፈሉ ከዚህም እጅግ ወርደው ገሊላዊ ናዝራዊ እንዲባባሉ ያበቃቸው ከአህዛብ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ፈር ባለማስያዛቸው ነበር፡፡ ፈሪሳዊያን ደግሞ ሕግን በማጥበቅ ሕዝቡን የሚያስመርሩ ቀሚሳቸውን በማስረዘም እነሱ የማይፈጽሙትን ሕግ በሕዝብ ላይ የሚጭኑ ራሳቸውን ከሌሎች በላይ ከፍ ከፍ የሚያደርጉ አባታችን አብርሐም እያሉ የሚመጻደቁ የአባታቸው የአብርሐምን ስራ ግን የማይሰሩ ክፍሎች ናቸው ዮሐ 8-39፡፡ ታዲያ ኒቆዲሞስ ምንም እንኳ ከፈሪሳዊያን ወገን ቢሆንም ራሱን ከዚህ ሕዝብ ለይቶ ክርስቶስን ፍለጋ በፍጹም ልቡ የመጣ ፈሪሳዊ ነው፡፡ ቀድሞ አባታችን አብርሀምን ከቤተሰብህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ ያለው አምላክ ኒቆዲሞስን ከፈሪሳዊያን ለይቶ ጠራው፡፡ ዘፍ 12

፪. ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ ነው ዮሐ 3-1

ሮማውያን ሕዝቡን የሚያሥተዳድሩት ከላይ ያለውን ዋና ሥልጣን ተቆናጠው ታች ያለውን ሕዝብ ደግሞ ባህላቸውን በሚያውቅ ቋንቋቸውን በሚጠነቅቅ አይሁዳዊ ምስለኔ ነው፡፡ አውሮፓውያንም አፍሪካን ለመቀራመት የተጠቀሙበት ስልት ይህን ዓይነት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስም ምንም እንኳ ፈሪሳዊ ቢሆን አለቃ እንዲሆን በሮማውያን የተሾመ ባለሥልጣን ነው፡፡

፫. ኒቆዲሞስ መምህረ እስራኤል ነው ዮሐ 3-10

ጌታ ምስጢረ ጥምቀትን በገለጸለት ጊዜ ሲደናገር አይቶ «አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን? » ብሎታል፡፡ ይህ የሚጠቁመን ኒቆዲሞስ አለቅነትን ከመምህርነት የያዘ በአይሁዳውያን የታፈረና የተከበረ ሰው እንደነበረ ነው፡፡ መምህር ቢሆንም የሚቀረኝ ያላወቅሁት ያልጠነቀቅሁት ብዙ ነገር አለ በማለት የመምህርነቱን ካባ አውልቆ የተማሪነትን ዳባ ለብሶ ከክርስቶስ ሊማር መጣ፡፡

፬. ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት ነው ዮሐ 7-51
አንዳንዴ ሳያውቁ አወቅን ሳይማሩ እናስተምር የሚሉ ደፋር መምህራን አይጠፉም፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ከዚህ በተለየ አለቅነትን ከመምህርነት መምህርነትን ከምሁርነት አስተባብሮ የያዘ ዕውቀትን ከትህትና ምሁርነትን ከደፋርነት አንድ አድርጎ የያዘ ሰው ነበር፡፡ የኦሪት ምሁር መሆኑን የሚጠቁመን ደግሞ ከካህናት አለቆች ጋር ያደረገውን ክርክር ባስታወስን ጊዜ ነው፡፡

ኒቆዲሞስ ምን አደረገ?

ለምስጢረ ጥምቀት መገለጥ ምክንያት ሆነ ዮሐ 3 1-21

የአይሁድ የፋሲካ በዓል እየቀረበ ሲመጣ ክርስቶስ ቀኑ እንደደረሰ ለሐዋርያቱ ተናግሮ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡ እንደ ሰውነቱ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይል ሕዝቡን ቀንና ሌሊት በትምህርትና በተዐምራት ያገለግል ነበር፡፡ በዚህ ሰዐት ነው ኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው፡፡ በፊቱ ቀርቦም «መምህር ሆይ » ብሎ የእርሱን አላዋቂነት የክርስቶስን ማእምረ ኅቡዐትነት (የተሰወረን አዋቂነት) መሰከረ፡፡ ጌታችንም አመጣጡ ከልብ መሆኑን አውቆ ምሥጢረ ጥምቀትን (ዳግም ውልደትን) ገለጸለት፡፡ ምስጢሩ የኦሪት ምሁር ለነበረው ኒቆዲሞስ ለጆሮ የከበደ ለመቀበል የሚቸግር ሆነበት፡፡ የከበደውን የሚያቀል የጠበበውን የሚያሰፋ አምላክ ምሥጢሩ ለኒቆዲሞስ እንደከበደው ስለተረዳ ቀለል አደረገለት፡፡ ዳግም ውልደት ከእናት ማኅፀን ሳይሆን ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ እንደሆነ አብራራለት ፡፡

አዋቂ ነን የሚሉትን አሳፈራቸው ዮሐ 7-51

ወቅቱ የአይሁድ የፋሲካ በዓል የቀረበበት ጻፎችና የካህናት አለቆች ጌታን ለመያዝ፣ እንደሙሴም ህግ ሊያስፈርዱበት የቋመጡበት ጊዜ ነበር፡፡ የሙሴ ፈጣሪ መሆኑን መቸ አወቁና? የካህናት አለቆች ተሰብስበው ክርስቶስን ለመያዝ በሚመካከሩ ጊዜ ከሙሴ መጽሐፍ ሕግ ጠቅሶ ሊቃውንተ ኦሪትን አፍ ያስያዛቸው እሱ ነበር፡፡በዚህም የተነሳ ሳይስማሙ ወደየቤታቸው እንዲበታተኑ ምክንያት የሆነ ታላቅ ሰው ነው፡፡

ጌታን ለመገነዝ በቃ ዮሐ 19-38

ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ ራሱን ለዓለሙ ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ እስከ ሞት ከአንተ አንለይህም ያሉት ደቀ መዛሙርቱ ሲበታተኑ ፣ከዮሐንስ በቀር ፣በዘጠኝ ሰዐት ቀራንዮ የነበረ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ሆኖ የክርስቶስን ስጋ ከአለቆች ለምኖ፣ የገነዘ፣የክርስቶስን ክቡር ሥጋ ከርቤና የእሬት ቅልቅል ያርከፈከፈለት ወደ ሐዲስ መቃብር ያወረደውም ኒቆዲሞስ ነበር፡፡
ከኒቆዲሞስ ምን እንማር?

አትኅቶ ርእስ

በቅዱስ ወንጌል ላይ በተደጋጋሚ የምናገኘው የፈሪሳውያንን ግብዝነትና የጌታችንን ተግሳጽ ነው፡፡ ማቴ 9 10፣ ማቴ 23፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነን የፈሪሳዊውና የቀራጩ ጸሎት ምን ይመስል እንደነበር መመልከት ነው ሉቃ 18 9፡፡ ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ፣ የአይሁድ አለቃ ፣መምህረ እስራኤል ፣ምሁረ ኦሪት ቢሆንም ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታ እግር ስር ቁጭ አለ፡፡ ሕዝብን ከመምራትና ከማስተማር ይልቅ ቁጭ ብሎ መማር ምንኛ መታደል ነው! ጌታስ በትምህርቱ «ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርሷም አይወሰድባትም » ያለ ለዚህ አይደል ሉቃ 10 42፡፡ ብዙዎቻችን ባለን የኑሮ ደረጃ የዕውቀት ደረጃ የስልጣን ደረጃ ራሳችን ሰቅለን የመማር አቅም አጥተናል፡፡ ቁጭ ብሎ መማር ደረጃችንን የማይመጥን የሚመስለንስ ስንቶች እንሆን? አንድ ወቅት አባ መቃርስ ከህጻናት እንቆቅልሽ ለመማር ቁጭ እንዳሉ በእንቆቅልሹም ልባቸው ተነክቶ እያነቡ ወደ በዐታቸው መመለሳቸውን እያወቅን የመማር አቅም ያጣን ስንቶች እንሆን? ማን ያውቃል ከአንድ ሰአት ስብከት ውስጥ እግዚአብሔር ሊያስተመረን የፈለገ አንዲት ዐረፍተ ነገር ቢሆንስ? ትሑት የሚያሰኘው ሳያውቁ አላውቅም ማለት ሳይሆን እያወቁ አላውቅም ማለት ነው፡፡ ሳይማሩ ተምሬያለሁ ማለት ሳይሆን ተምረውም ልክ እንደ ኒቆዲሞስ ለመማር ራስን ዝቅ ማድረግ ነው፡፡

ጎደሎን ማወቅ

መምህርም ምሁርም ሆኖ ቁጭ ብሎ መማር ምን ረብ አለው? ይባል ይሆናል፡፡ ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት እንጅ ምሁረ ሐዲስ አይደለም ኒቆዲሞስ መምህረ እስራኤል ዘስጋ እንጅ መምህረ እስራኤል ዘነፍስ አይደለም፡ ክርስትና አለቃና ባሪያን አንድ እንደምታደርግ አያውቅምና የጎደለውን ፍለጋ መጣ ገላ 3 26፡፡ ያለውን ሳይሆን ያጣውን የሞላለትን ሳይሆን የጎደለውን ፍለጋ መጣ፡፡ዕውቀት ብቻውን ምሉእ አያደርግም፡፡ አለቅነትም ቢሆን ገደብ አለው፡፡የሕይወቱን ክፍተት ሊሞላ የሚችል አንድ ክርስቶስ ብቻ ነውና ጎደሎነቱን አምኖ መጣ፡፡ የሚጎድለኝ ምንድን ነው? ብሎ እንደጠየቀው እንደዚያ ሰው ጎደሎን ማመን ምንኛ ታላቅ ነገር ነው ማቴ 18 21፡፡ በአብዛኞቻችን የሚታየውና ክርስትናችንን አገልግሎታችንን ቤተክርስትያናችንን እየተፈታተነ ያለ ችግር ጎደሎዎቻችንን አለማወቅና ምሉእ ነኝ ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ምንም እንዳልሆኑ አውቆ ራስን ለክርስቶስ፣ ራስን ለመርዐተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አሳልፎ መስጠት ምንኛ መታደል ነው!

አልዕሎ ልቡና (ልቡናንን ከፍ ማድረግ)

ኒቆዲሞስ ይዞ የመጣው ስጋዊ ህዋሳቱን ነበር፡፡ጌታችን ግን አመጣጡ ለመልካም እንደሆነ አውቆ ለስጋዊ ዕውቀት እጅግ የሚከብደውን ምስጢረ ጥምቀትን ገለጸለት፡፡ መጀመሪያ ይህን ምስጢር ለመቀበል አልተቻለውም ነበር፡፡ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ምስጢሩን ፍንትው አድርጎ ሲያብራራለት ግን ልቡናው ይህን ምስጢር ለመቀበል ከፍ ከፍ አለ፡፡ ምስጢራትን ለመቀበል ልቦናን ከፍ ከፍ ማድረግ ይገባል፡፡የእምነታች መሰረት በስጋ ዓይን ማየት በስጋ ጆሮ መስማት በስጋ እጅ መዳሰስ ብቻ ከሆነ ልክ እንደ እንቦይ ካብ ሆነ ማለት ነው፡፡ ትንሽ ነፋስ ትንሽ ተፅዕኖ ሲያርፍበት መፈራረስ መናድ ይጀምራል፡፡ ኒቆዲሞስም ምስጢሩ መጀመሪያ ቢከብደውም ቅሉ በኋላ ላይ ልቦናውን ወደ ሰማያዊው ምስጢር ከፍ ስላደረገ ምስጢሩ ተገለጸለት፡፡ ቤተክርስቲያንን ሲፈታተኗትና እየተፈታተኗት ያሉ አካላት በሙሉ የስህተታቸው ምንጭ እንደ ግያዝ ከአካባቢያቸውና ከምናየው አካል (ቁሳዊ ዓለም) ውጭ መመልከት አለመቻል ነው 2ነገ 6- 17፡፡ ለዚህም ነው ካህኑ በስርዓተ ቅዳሴ ጊዜ የቁርባኑ ምስጢር እንዲገለጽልን «አልዕሉ አልባቢክሙ (ልቦናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ)» የሚሉን፡፡

የእውነት ምስክር (ስምዐ ጽድቅ) መሆን

ኒቆዲሞስ ያለፍርሐትና ያለ ሃፍረት በካህናቱ ፊት እውነትን መስክሯል፡፡እውነትንና ፀሐይን ፈርቶ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ካህናቱን መጽሐፍ ጠቅሶ እውነትን ተናግሮ አሳፍሯቸዋል፡፡ በመሪዎች ፊት በታላላቅ ሰዎች ፊት እውነትን መመስከር ክርስትናችን የሚያስገድደን ቁም ነገር ነው ሉቃ 12 8፡፡ ቤተክርስቲያን ሰማዕታት እያለች የምትዘክራቸው በሙሉ ለእውነት ብለው ራሳቸውን ለክርስቶስ አሳልፈው የሰጡ ቅዱሳንን ነው፡፡በፍርሐትና በሀፍረት በይሉኝታና በሀዘኔታ እውነትን አለመመስከር በክርስቶስ ፊት ያስጠይቃል እንጅ አያስመሰግንም ማቴ 10 32፡፡ «ለእውነት እንጅ በእውነት ላይ ምንም ማድረግ አንችልም» እንዳለ 2ቆር 13 8፡፡

ትግሃ ሌሊት

እንደ ሌሊት ለመንፈሳዊ ህሊና ለተመስጦ የሚመች ጊዜ የለም ፡፡ ቀን ለስጋ ሲራወጥ የነበረ አካልና መንፈስ ሌሊቱን ለነፍስ በምገዛት ስጋውን መጎሰም አለበት፡፡ ለዚህም ነው ቅድስት ቤተክርስቲያን ቀኑን በቅዳሴ ሌሊቱን ደግሞ በማኅሌት በሰዓታት በኪዳን እግዚአብሔርን ስታምሰግን የምታድረው፡፡ ቅዱስ ማር ይስሐቅ ሌሊትስ ጌታን ለማመስገን የተፈጠረ ድንቅ ጊዜ ነው ያለው፡፡ ጌታችንም ሐዋርያቱን ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ ብሏቸዋል ማቴ 26፡፡ አሁንም ቤተክርስቲያን እንደ ኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ ለኪዳን ለማኅሌት ለጸሎት የሚመጣን ምዕመን ትፈልጋለች፡፡

እስከ መጨረሻ መጽናት

ጌታችንን በመዋዕለ ስብከቱ ብዙ ሺህ ሕዝብ ቢከተለውም እስከመስቀሉ አብረውት የነበሩ ጥቂቶች ናቸው፡፡ የተወሰነው ሕዝብ ቀድሞም የተከተለው ለምግበ ስጋ ነበርና ቀራንዮ ላይ አልተገኘም፡፡ ቀራንዮ ላይ ምግበ ነፍስ እንጅ ምግበ ስጋ የለም፡፡ ሌሎችም በቤተሰብ በሀብት በፍርሀት ምክንያትነት መስቀሉ ስር አልተገኙም፡፡ ምንም እንኳ ኒቆዲሞስ በስድስት ሰዐት ባይገኝም የክርስቶስ ስጋ ከነፍሱ በምትለይበት ሰዐት ክርስቶስን ከመስቀል አውርዶ ለሐዲስ መቃብር ያበቃው እሱ ነበር፡፡ በዚህ የመከራ ሰዐት ከዮሐንስና ከእናቱ ከድንግል ማርያም ውጭ ማንም እንዳልነበረ መጻሕፍት ከገለጹልን በኋላ የምናገኛቸው የቁርጥ ቀን ልጆች ዮሴፍንና ኒቆዲሞስን ነው፡፡ ይህም ፈተናውን ሁሉ ተቋቁሞ እስከ መጨረሻው ለመጽናቱ ምስክር ነው፡፡ በክርስትና ሕይወታችንም የምናያቸው ነገሮች ከዚህ የተለዩ አይደሉም፡፡በምቹ ጊዜ የምናገለግል ፈተና ሲመጣ ጨርቃችን(አገልግሎታችንን) ጥለን የምንሮጥ ማር 14-51 ሰበብ አስባብ ፈልገን የምናፈገፍግ ብዙዎች ነን፡፡ ዕውቀት ጣዖት ሆኖበት መሀል መንገድ የቀረው ሀብት ጣዖት ሆኖበት ሩጫ ያቋረጠውን ጊዜ ጣዖት ሆኖበት ቅዳሴ የሚቀረውን ቆጥረን እንጨርሰው ይሆን? ጌታ በትምህርቱ «ለዘአዝለፈ ትዕግስቶ ውእቱ ይድኅን -እስከ መጨረሻው የሚፀና እርሱ ይድናል » እንዳለ ማቴ 2413፡፡ ክርስትና ለጀመሩት ሳይሆን ለጨረሱት ለወጠኑት ሳይሆን ለፈጸሙት የድል አክሊል የምትሰጥ መንገድ እንጅ የመሮጫ መሙን ጠበበን ሩጫው ረዘመብን ለሚሉ ዴማሶች ቦታ የላትም፡፡2ጢሞ 4-9

በአጠቃላይ ከኒቆዲሞስ ህይወት ብዙ ቁምነገሮችን እንማራለን፡፡ የኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ መምጣት ለምስጢረ ጥምቀት ትምህርት መገለጥ ምክንያት እንደሆነ ሁሉ በቅዳሴው በኪዳኑ በሰዓታቱ በማኅሌቱ መገኘትና መሳተፍ ረቂቅ የሆነው ሰማያዊ ምሥጢር ፍንትው ብሎ አንዲገለጥልን ምክንያት ነውና በምሥጢራት በመሳተፍ ራስን ዝቅ በማድረግ ለታላቅ ክብር እንድንበቃ የእርሱ መልካም ፈቃድ ይሁንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ገብርሔር


ዛሬ ታላቁን የጌታችንን ጾም ከጀመርን ስድስተኛ ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህን ሳምንት ቅድስት ቤተክርስቲያን «ገብርሔር» የሚል ስያሜ ሰጥታዋለች፡፡ ገብርሔር በጎ አገልጋይ ማለት ሲሆን የስያሜውን መነሻ የምናገኘው በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው የወንጌል ክፍል ማቴ.25-14-30 ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ መስሎ ካስተማራቸው ትምህርቶች መሀከል አንዱ የሆነው ይህ የዛሬው ወንጌል አስተማሪ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን በውስጡ ይዟል፡፡ በተለይ ምንም እንኳን የቤተክርስቲያን ሓላፊነት የእገሌና የእገሊት ተበሎ ባይወሰንም ቅሉ ቤተክርስቲያን ባላት የአገልግሎት መዋቅር መሠረት የሓላፊነትን ቦታ ይዘው ለሚያገለግሉ ሰዎች አትኩሮት ሊሰጡባቸው የሚገባቸውን ነጥቦች ይጠቁማል፡፡ ይህን ለማየት ያመቸን ዘንድ ከታሪኩ የመጀመያ ክፍል በመነሣት ዋና ዋና የሆኑ አሳቦችን በአትኩሮት መመርመር ጠቃሚ ነው፡፡

በምሳሌያዊው ታሪክ መጀመሪያ ላይ የምናገኘው አንድ መንገድ ሊጀምር ያሰበ ሰው ከመሔዱ በፊት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን ለአንዱ አምስት ለአንዱ ሁለት እንዲሁም ለሌላኛው አንድ መክሊት ነግደው ያተርፉበት ዘንድ እንደሰጣቸው ነው፡፡

ገና ከታሪኩ መጀመሪያ እንደምንረዳው የአገልጋዮቹ ጌታ ምንም እንኳን እርሱ ለመንገድ ቢዘጋጅም ሀብቱ ግን በተዘጋ ቤት ውስጥ ተቆልፎበት እንዲቀመጥ አልፈለገም፡፡ በዚህም አገልጋዮቹን ጠርቶ ገንዘቡን በአደራ ተቀብለው «እንዲያተርፉበት» ማዘዙን እንደማስረጃ ልናቀርብ እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን ማትረፍ በመፈለጉ ብቻ ገንዘቡን ያለአግባብ አልበተነም፡፡ ነገር ግን ለእርሱ ቀረቤታ የነበራቸውን አገልጋዮቹን ጠርቶ ያውም እንደየችሎታቸው መጠን ሓላፊነቱ ሳይከብዳቸው እንዲሠሩበት ገንዘቡን አከፋፈላቸው፡፡

ይህ ጌታ ቅንነትና ርኅራኄ የበዛለት እንደሆነ የሚያመላክተን ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለአገልጋዮቹ ሓላፊነትን ቢሰጥም እንኳን ከእነርሱ ጋር በነበረው ቀረቤታ ማን ምን መሥራት ይችላል የሚለውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዳቸው እንደ ሓላፊነት የመሸከም አቅማቸው አምስት ሁለት አንድ እያደረገ መስጠቱ ነው፡፡

ምናልባት ስስት ባልተላቀቀው ስሜት ለሚያስብ ሰው የዚህ ጌታ መክሊት አሰጣጥ አድልዎ ያለበት ሊመስለው ይችላል፡፡ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ብንከታተለው ግን የሚያሳየን የባለ መክሊቱን ባለቤት ቅንነት ነው፡፡ ቀጥለን እንደምናነበው ይህ ጌታ ለአገልጋዮቹ አትርፉበት ብሎ መክሊቱን ሰጥቷቸው በሔደበት ሀገር አልቀረም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ በተሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው እንደመጣ እናነባለን፡፡ ስለዚህ አገልጋዮቹ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩ እንደሚጠይቃቸው እያወቀ ከአቅማቸው በላይ የሆነ መክሊትን በመስጠት ምን ሠርተው የተሰጣቸውን መክሊት ያህል ማትረፍ እንደሚችሉ በማሰብ እንዲጨነቁ አልፈለገም፡፡ በተቃራኒው የምናየው ያለምንም ጭንቀት ከአእምሯቸው በላይ ሳይሆን ባላቸው ኃይል ተጠቅመው መሥራትና ማትረፍ የሚችሉትን ያህል መክሊት እንደሰጣቸው ነው፡፡

ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው ሲመጣ አምስት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ አምስት እንዲሁም ሁለት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ ሁለት መክሊት አትርፎ ጌታቸው ፊት እንደቆሙ ያ ጌታም በእነዚህ አገልጋዮቹ ታማኝነት ተደስቶ ወደ ደስታው እንዳስገባቸው እናያለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ያ አንድ መክሊት ተቀብሎ የነበረው ምድርን ቆፍሮ ያተርፍባት ዘንድ የተሰጠችውን መክሊት እንደቀበረ ከዚህም አልፎ ምን አደረክባት ተብሎ ሲጠየቅ የአመጽ ንግግር እንደተናገረ በዚህ ከፊቱ ያዘነው ጌታውም ያን ክፉ አገልጋይ እንዲቀጣ እንዳደረገው አናነባለን፡፡

በዚህኛው ክፍል ከተጠቀሰው ታሪክ ሦስቱን አካላት ማለት የመክሊቱን ሰጪ ጌታ፣ በጎ የተባሉ አገልጋዮችና ክፉ እና ሰነፍ የተባለውን አገልጋይ በተናጥል እንመልከታቸው፡፡

1. የአገልጋዮቹ ጌታ፡-

ይህ ሰው ለገንዘቡ ጠንቃቃ ከመሆኑ ባሻገር በአገልጋዮቹ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው እናያለን፡፡ በክፉው አገልጋይ ላይ ባለመታዘዙ ምክንያት የፈረደበትን ፍርድ /ልቅሶና ጥርስ ማፏጨት ወዳለበት በውጪ ወዳለ ጨለማ አውጡት/ ስንመለከት የሚያሳየን የአገልጋዮቹን ጌታ ታላቅ ሥልጣን ነው፡፡ ምንም እንኳን ሥልጣኑ ጽኑ ቢሆንም ይህ ጌታ ፍርዱ ግን በእውነት ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ደግሞ በድካማቸው ታግዘው በተሰጣቸው መክሊት ላተረፉት በጎ አገልጋዮች የሰጣቸውን ፍጹም ደስታ መጥቀስ ይቻላል፡፡

2. በጎ አገልጋዮች:-

በአገልጋዮቹ ጌታ በጎ አገልጋዮች የተባሉት አምስት መክሊት የተቀበለውና ሁለት መክሊት የተቀበለው ናቸው፡፡ እዚህ ጋር ማስተዋል የሚገባው እነዚህ ሁለቱ አገልጋዮች በጎ አገልጋዮች ለመባል ያበቃቸው አስቀድመው ብዙ ወይንም የተሻለ ቁጥር ያለው መክሊት ለመቀበል መብቃታቸው አይደለም፡፡ ጉዳዩ የመክሊቱ ቁጥር ሳይሆን በተሰጣቸው መክሊት መጠን የሚገባቸውን ያህል ደክመው ማትረፍ መቻላቸው ነው፡፡ ወይንም ያ ባለ አንድ መክሊት አገልጋይ ከሁለቱ ያሳነሰው ከአንድ በላይ መክሊት መቀበል የማይችል መሆኑ ሳይሆን በዚያችው በአንዷ መክሊት እንኳን መሥራት አለመቻሉ ነው፡፡

3. ክፉና ሰነፍ አገልጋይ:-

ይህ ሰው የተጠቀሱ ሦስት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡
ሀ. የአገልጋዮቹ ጌታ ወደ መንገድ ሊሔድ በተዘጋጀበት ወቅት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደችሎታቸው ገንዘቡን ሲሰጣቸው አትርፈው እንዲቆዩት ነው፡፡ ከላይ እንደተነገጋገርነው እንደ አቅማቸው መስጠቱም አቅማቸው በሚፈቅደው የሥራ ደረጃ እንዲሰማሩ በማሰብ ነበር፡፡ ይህ ሰነፍ አገልጋይ ግን ያደረገው ከታዘዘበት ዓላማ በተቃራኒው መልኩ ነው፡፡ ሊሠራበት የሚገባውን መክሊት ቀበረው፡፡ ይህም ለጌታው ትዕዛዝ ያለውን ቸልተኝነት ያሳያል፡፡

ለ. ጌታው በመጣ ጊዜ አመጽ የተመላበት የሐሰት ንግግር ተናግሯል፡- ከሔደበት ቦታ ተመልሶ ጌታው በተሰጠው መክሊት ምን እንዳደረገ ሲጠይቀው «አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበሰብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ ስለፈራሁም ሔድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፡፡» ሲል መለሰለት፡፡ ይህ ንግግር ከአመጽ ንግግርነቱ በተጨማሪ ውሸት አለበት፡፡ ምክንያቱም እርሱ እንዳለው ጌታው ካልዘራበት የሚያጭድ ካልበተነበት የሚሰበሰብ ጨካኝ ሰው ቢሆን ኖሮ ያደርግ የነበረው ምንም መክሊት ሳይሰጠው ከነትርፉ ሁለት መክሊቶችን ይጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ተጽፎ የምናነበው ትርፉን ከመጠየቅ በፊት አንድ መክሊት ሰጥቶት እንደበረ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አስቀድሞ ገንዘቡን ዘርቶ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጌታ ዘርቷልና ማጨድ ይገባዋል፤ በትኗልና መሰብሰብም መብቱ ነው፡፡

ሐ. እርሱ መሥራት ሲሳነው እንኳን ዕድሉን ለሌሎች አልሰጠም፡- ይህ ሰው የተሰጠው መክሊት በትርፍ ሊመለስ እንደሚገባው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ምክንያቱም ገና ሲቀበል ከጌታው የተቀበለው ትዕዛዝ ነውና፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን መውጣት መውረዱ ቢከብደውም ወጥተው ወርደው ማትረፍ ለሚችሉ ሰዎች አለመስጠቱ ተጨማሪ ጥፋቱ ነው፡፡ ይህን እንዳያደርግ ያሰረው ደግሞ ውስጡ የተቀረጸው የአመጽ መንፈስ ነው፡፡ ጌታው መጥቶ ስለ ትርፉ ሲጠይቀው የሚመልስለትን ረብ የለሽ ምክንያት እንደ መከላከያ አድርጎ ማሰቡ አእምሮው ሌላ አማራጭ እንዳያስብ የዘጋበት ይመስላል፡፡

የመጽሐፈ ቅዱስ መተርጉማን አባቶች የዚህን ምሳሌያዊ ታሪክ ምስጢር ሲያስተምሩ የአገልጋዮቹ ጌታ የፍጡራን ጌታ የሆነ የእግዚአብሔር ምሳሌ እንደሆነ እንዲሁም ሦስቱ አገልጋዮች በተለያየ ደረጃ ያሉ ምዕመናንን እንደሚወክሉ ያስተምራሉ፡፡

ከዚህ የወንጌል ክፍል ምን እንማራለን?

ከተጠቀሰው ታሪክ የምንማራቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም አበይት የሆኑትን ሁለቱን እንመልከታቸው፡፡

1. ለእያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ እንዳለ እንረዳበታለን

እግዚአብሔር እያንዳንዳችን በሃይማኖት ሆነን የምናፈራውን ፍሬ ይፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን ከእኛ ፍሬን ቢፈልግም ያን ፍሬ ማፍራት የምንችልበትን ኃይል ግን የእግዚአብሔርን ልጅነት ካገኘንበት ከዕለተ ጥምቀት ጀምሮ እንደሚያስፈልገን መጠን እየሰጠን ነው፡፡

ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበልናቸው ስጦታዎች በቁጥር እጅግ ብዙ ቢሆኑም በአይነታቸው ግን ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው እያንዳንዱ ክርስቲያን ዳግመኛ በመወለድ ምስጢር ያገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት ጸጋና ከልጅነት ጋር በተያያዘ የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው ፡፡ዮሐ.3-3 ሁለተኛው አይነት ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና እንደ ሰውየው አቅም ለተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ማስፈፀሚያ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔር የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ትንቢት መናገር ፣ በተለያዩ ልሳናት መናገር ፣ አጋንንትን ማስወጣት ... የመሳሰሉት ከዚህኛው አይነት ስጦታ የሚመደቡ ናቸው፡፡ 1ኛ ቆሮ.12-4፡፡

በመጀመሪያውም ይሁን በሁለተኛው አይነት ስጦታ ተቀባዮች ዘንድ ግን ብዙ የሚያሳዝኑ ችግሮች አሉ፡፡ በዳግመኛ መወለድ ምሥጢር (በ40 ና 80 ቀን ጥምቀት) ስላገኘነው የልጅነት ጸጋ ጊዜ ሰጥቶ የሚያስብ ክርስቲያን ማግኘት በዚህ ዘመን በጣም አዳጋች ነው፡፡ በዓመት ውስጥ ክርስቲያንነቱ ለጥምቀት በዓልና ለመስቀል ደመራ ካልሆነ ትዝ የማይለው ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ከቤተ ዘመድ አንድ ሰው ምናልባትም ራሱም ሊሆን ይችላል ነፍሱ ከሥጋው ካልተለየች ወደ ቤተ ክርስቲያን ደጅ ብቅ አይልም፡፡

እግዚአብሔር ለእኛ የልጅነትን ጸጋ በመስጠቱ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅሩን አሳይቶናል፡፡ ምክንያቱም ልጅነታችን ዋጋ ተከፍሎበታልና፡፡ እንዲሁ በቀላሉ አይደለም ልጆች የተባልነው፡፡ እኛ ልጅነትን እንድንቀበል አምላክ መከራን ተቀብሏል፡፡ የጥምቀታችን ውሃ የፈሰሰው በጦር ከተወጋው ከጌታ ጎን ነው ፡፡ ዮሐ.19-24፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይሄንን ሁሉ ሲያመለክት ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ፡፡›› 1ኛ ዮሐ.3-1 ያለው፡፡

እኛ ልጆቹ እንሆን ዘንድ እግዚአብሔር ካሳየን የአባትነት ፍቅር በተጨማሪ ልጆቹ ስለመሆናችን የገባልንም ተስፋ ከአዕምሮ በላይ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምዕመናን በላከው መልእክቱ ‹‹እንኪያስ እናንተ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፡፡ ልጆች ከሆናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ፡፡›› ገላ.4-7 ስለሚጠብቀን ተስፋ ነግሮናል፡፡

ትልቁ ችግር ግን ተጠማቂው ሰው ይህን የልጅነት ክብር አለመረዳቱ ነው፡፡ የልጅነቴን ክብር ተረድቻለሁ እያለ የሚያወራውም ቢሆን የልጅነቱን መክሊት በልቡናው ውስጥ ቀብሮ አንድም ፍሬ ሳያፈራ ስለማንነቱ ለማውራት ቃላት ሲመርጥ ጊዜውን ያባክናል፡፡ አብዛኛው ግን የክርስትና እምነት ደጋፊ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅነት ሊገለጥ የሚገባው እንደ ሀገር ልጅነታችን በምናሳየው የደጋፊነት /የቲፎዞነት/ ስሜት አይደለም፡፡ ደጋፊነት በጊዜ ና በቦታ ለተወሰነ ያውም ኃላፊ ለሆነ ድርጊት ነው፡፡ ክርስትና ግን በማንኛውም ቦታ፣ ጊዜ የሚኖርበት የህይወት መስመር እንጂ የሚደገፍ ጊዜያዊ ድርጊት አይደለም፡፡

ስለዚህ በጣም ልንጠነቀቅበት የሚገባን የመጀመሪያው መክሊታችን ልጅነታችን መሆኑን መረዳት ያስፈልገናል፡፡በዚህም መክሊት እንድንሰራ የታዘዝናቸውን ምግባራት እንድናፈራ የሚጠበቅብንን ፍሬዎች ማፍራት አለብን፡፡ ያለበለዚያ መክሊቱን እንደቀበረው ሰው መሆናችን ነው፡፡

2. እያንዳንዱ ስጦታ እንደሚያስጠይቅ እንረዳለን

እግዚአብሔር ያለ አንድ አላማ ለሰዎች ኃላፊነትን የሚያሰከትል ስጦታ አልሰጠም አይሰጥምም፡፡ ማንም ከእግዚአብሔር የተቀበለ ሰው የተሰጠው ስጦታ ለሆነ አላማ ነውና ጥያቄ አለበት፡፡ ጠያቂው ደግሞ የስጦታው ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

መንጋውን እንዲጠብቁለት ሥልጣንና የተለያዩ የአገልግሎት ሰጦታዎችን እግዚአብሔር የሰጣቸው አሉ፡፡ዮሐ. 21-15 ፤ ገላ.1-15-16፡፡ ሆኖም ግን የተሰጣቸው ኃላፊነት የሚያስጨንቃቸው፣ ከልባቸው በእውነተኛ ትህትና የሚተጉ ያሉትን ያህል የሚያገለግሉበትን ስጦታ ከእግዚአብሔር መቀበላቸውን እንዲሁም የሚያስጠይቃቸው መሆኑን እስኪዘነጉ ድረስ መንገዳቸውን የሳቱ አሉ፡፡ በእግዚአብሔርና በሰዎች መሀከል እንደ ድልድይ ሆነው ያገለግሉበት ዘንድ በተሰጣቸው ሥልጣን እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ተግባር የሚፈፅሙ ሰዎች ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

እንዲሁም ደግሞ ተሰባኪውን ወደ እግዚአብሔር ከመምራት ይልቅ የነሱ ደጋፊ፣ ስለክብራቸው ተሟጋች እንዲሆን በህዝቡ መሀከል ጎራ እንዲፈጥርና የጳውሎስ ነኝ የአጵሎስ ነኝ እንዲል የሚያደርጉት ሰባኪዎችም ሌሎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ማንም ይሁን ማን ግን ስለተሰጠው መክሊት ባለቤቱ ከፊቱ አቁሞ እንደሚጠይቀው መዘንጋት የለበትም፡፡


በዲ/ን አባተ አስፋ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ደብረ ዘይት

እንኳን ለጾመ እኩሌታው /ለደብረ ዘይት/ በሰላም አደረሳችሁ፡፡
ደብረ ዘይት

ብዙዎች በስሜ ይመጣሉ /ማቴ.24.1-36/


የዐቢይ ጾም አምስተኛው ሳምንት ደብረ ዘይት ይባላል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በደብረዘይት ነገረ ምጽአቱን እንዳስተማረ የሚነገርበት ሳምንት ነው፡፡ «ወእንዘ ይነብር እግዚእነ ውሰተ ደብረዘይት ቀርቡ ኀቤሁ አርዳኢሁ እንተበህቲቶም» ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ስምዖን፣ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ እንድርያስን ጨምሮ ቀርበው «ንገረን ይሄ መቼ ይሆናል?» በማለት ጥያቄ ጠየቁት፡፡ ጥያቄውም የዓለም መጨረሻውና የመምጫህ ምልክቱ ምንድን ነው? የሚል ነበር፡፡
ጌታችንም የዓለም መጨረሻውና ምልክቱን በዝርዝር አስረድቷቸዋል፡፡ እኛም ጊዜው ግድ ከሚለን አንፃር አጠር አድርገን ዋና ዋናዎችን እንመለከታን፡፡

- «ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ እኔ ክርሰቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎች ይስታሉ» የሚለው ኃይለ ቃለ የዓለምን መጨረሻ ከሚጠቁሙን ዋና ምልክቶች መካከል አንዱ የብዙዎች በስሙ መመጣት ነው፡፡ ይህም ከዚህ በፊት በዓለም ላይ ብዘዎች «እኔ ክርስቶስ ነኝ» ብለው የመጡ አሉ፡፡ ከዚህ በከፋ መልኩ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንኳ በየመንደሩ በክርስቶስ ስም የሚፈለፈሉ የእምነት መሳይ ድርጅቶች ዛሬ በሺዎች የሚቆጠሩ ሆነዋል፡፡ ስለዚህ ጌታችን በስሜ ይመጣሉ ማለቱ ለማስጠንቀቂያ በመሆኑ ሰዎች ተሰነካክለው እንዳይወድቁ ለማሳሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ስለ ሃይማኖት እውቀቱም ብቃቱም ሳይኖራቸው ክርሰቶስ በሕልም በራዕይ ተገለጠልኝ በማለት ሰይጣን የሚጫወትባቸው ብዘዎች ስለሆኑ ሌላው ማስተዋል አጥቶ እየተከተላቸው እንዳይስት ነው፡፡ ዛሬ ሰይጣናዊነት /Devilism/ እንኳ ክርስቶስን እንደመከተል የተቆጠረበት ጊዜ ነው፡፡

- «ጦርነም የጦርንም ወሬ ትሰማላችሁ» የኸም የአንድ ሀገር ሕዝብ ከሌላ የሀገር ሕዝብ፤ በአንድ ሀገር ውስጥ እርስ በርሱ በአንድ ቤተሰብ እንዲሁ መለያየትና መዋጋት በዓለም ይሰፍናል፡፡ የአንደኛውና የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ከዚያም በኃላ ያለው እልቂት የምጽአቱን ምልክት ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም የባሰ የእልቂት አይከሰትም ለማለት ምንም ማረጋገጫ የለንም ትንቢቱም የሚለው ይህ ጥቂት መሆኑንና ከዚህም የባሰ የትንቢት ማረጋገጫ መኖሩን ነው፡፡

- ወይም ራሀብ ቸነፍር የምድር መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፡፡ ይህም የሚያሳየው ከሀገራችን ጀምሮ ድሆች ሀገራትን ስንመለከት ረሀብ ይወራባቸዋል፡፡ የምድር መናወጥን ስናይ ለሁሉም ዓለም መኖሩን በየጊዜው የቴሌቨዥን መስኮቶች እያስረዱ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ ሌሎች የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ እልቂቶች በዓለማችን ላይ ሰፍነው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በአደጉ ሀገሮች ላይ የሚታየው የኑሮ ቀውስ ሁሉ የምጽአቱ መቃርብ ምልክት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን ይህ ገና የመጀመሪያው መከራ እንጂ ቀጣዩ ከዚህ የሚበልጥ መሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ ዋነኛው ደግሞ ሰዎች በረሀብ ነፍስ መምታታቸው ነው፡፡ ይህም ዓለም ዛሬ በሚዲያዎቹና በተለያየ መገናኛዎቹ እያደነቀ ያለው ዓለማዊነት በመሆኑ ዓለምን ወደ አንድ ባህል ለማሸጋገር /ግሎባለይዜሽን/ በሚል አሰተሳሰብ እግዚአብሔርን ማመን ትኩረት የማይሰጠው በመሆኑ አሁን ደግሞ መላው ዓለም እግዚአብሔርን እንዲዘነጋ እየተሠራ ነው፡፡ ዓለም ትኩረት የሚሰጠውና የሚያደንቀው ኳስ ተጫዎችን ፊልም ተዋናይን፣ ዘፋኝነትን ወዘተ መሆኑ ጊዜው መቅረቡን ያስረዳል፡፡

በመሆኑም ሰው ከቃለ እግዚአብሔር እጦት የተነሳ በረሀብ ነፍስ እየተጐዳ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህም በመጨረሻ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንድናጣና ገሀነመ እሳት እንድንወድቅ የሚያደርግ ነው፡፡

በተጨማሪም ስለኔ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፣ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኃል ፍቅር ትቀዘቅዛለች፣ ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው ወዘተ.. የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች ያዛሉ መልእክቶች አምላካችን አስተላልፉልናል ይህንንም በዝርዝር ብናይ በውስጣቸው ብዙ መልክቶች እናገኛለን፡፡ ዋናው ቁም ነገሩ ለምልክትነት የሚገለጸውን መከራና የክህደት ዜና ታግሶ በሃይማኖት መጽናት እጀግ ጠቃሚና ለመንግሥት ሰማያት የሚያበቃ ነው፡፡ የእግአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን፡፡ 

በአባ ዘሚካኤል

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Friday, April 19, 2013

ኑ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንስራ መ.ነህ 2:20

ሰላም እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን የተወደዳችው የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ያደራ ልጆች እንደምን ውላችዋል እንደምን አድራችዋል የቅዱስ እግዚአብሔር ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን
ይችን በጅማሬ ያለች ቤተ ክርስቲያንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የእናንተን እርዳታ እሻለን የአቅማችሁን በመርዳት የበረከቱ ተካፋይ እንድትሆኑ በማለት በቅድስት ድንግል ማርያም ስም እ
ማፅናለ ክብር ምስጋና ለመድሓኔአለም ይሁን የእናታችን የቅድስት ቅዱሳን የድንግል ማርያም በረከት ረዴት ከሁላችን ጋር ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን
የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል እኛም ባሪያዎቹ ተነስተን እንሰራለን.መጽ ነህምያ 2:20 —

ይህን ሚስኪን ምንም የሌለው ከ ሰባ የማይበልጡ ክርስትያን ያለዋት ቤተ ክርስትያን የሚሰራላቸው አጥተው በዋርካ ስር ምስለ ፍቅሩ ወልዳ አስቀምጠው ለ32 ዓመታት የኖሩ ወገኖቻችን እንመልከታቸው እንያቸው ከጎናችሁ አለን እንበላቸው፡፡ ህንፃ ቤተክርስቲያኑ እየተሰራ ሲሆን የቤተ ክርስቲያኑን ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በተቸላችሁ መርዳት ይቻላል..

ኑ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንስራ መ.ነህ 2:20… 

ቅዱስ እንጦንስ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር
 Commercial Bank of Ethiopia, Bomb Tera Branch. Account no. 1000017080249
 mobile +251911143653, +251911780816, +251910016008 
ክብር ምስጋና ለመድሓኔአለም ይሁን፡፡ለፍፃሜው አድርሶ የበረከቱ ተካፋይ ለመሆን ያብቃን፡፡በርቱ እመቤቴ ከነልጅዋ ትርዳችሁ ትርዳን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!


 

Tuesday, April 2, 2013

ጉዞ ወደ ላፍቶ ሌንቃ መድሐኔዓለም መጋቢት 22 ቀን በተሳካ ሆኔታ አደረገ፡፡

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! 
የተሳካ መንፈሳዊ ጉዞ 
“የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን” ነህ.2፡20
 በመጀመርያ ይህን ሁሉ ላደረገ ልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው እንላለን!! የቅዱስ እንጦንስ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማህበር ጉዞ ወደ ላፍቶ ሌንቃ መድሐኔዓለም መጋቢት 22 ቀን በተሳካ ሆኔታ አደረገ፡፡ በጉዞው ለተሳተፉ መንፈሳዊ ወንድሞች ፤ እህቶች ፤ እናቶች ፤ አባቶች ፤ህፃናት በጠቅላላ በማህበራችን ስም ምስጋናችንን እያቀረብን በጉዞው ላይ ከተነሱ ፎቶግራፎች ውስጥ የተወሰነውን አፕሎድ አድርገናል ይመልከቱአቸው ፡፡ የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን እዚህ ደርሷል የቀረው የፊኒሺንግ ሥራ ነው፡፡ የመድኃኔዓለምን ቤተ ክርስቲያን በእቃዎችም ሆነ በገንዘብ እንዲሁም በቦታው በመሄድ አገልግሎት በመስጠት ከበረከቱ ተሳታፊ መሆን የምትፈልጉ: የባንክ አካውንት ቁጥር 1000017080249 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መርካቶ፤ ቦንብ ተራ ቅርንጫፍ ቤተክርስቲያኗን በመርዳት በተጨማሪም በየትኛውም ቦታ ያለን ምዕመናን ሁሉ በፀሎት፣ በጉልበት፣ ጥሬ ዕቃ በማቅረብ፣ የበኩላችንን እንድንወጣ መንፈሣዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በእነዚህ ስልክ ደውሉ ፡ +251911 14 36 53 +251911 24 90 37 +251911 53 41 97 +251910 01 60 08 ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን !

ቤተ ክርስትያናቸው በአሕዛብ ሲቃጠል ለ34 ዓመታት ይህል በዋርካ ስር የምናየውን ስእለ አድህኖ ይዘው አምላካቸውን ሲያመልኩበት እስከዚች ሰዓት ቆይተዋል