Monday, January 14, 2013

ኑ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንስራ መ.ነህ 2:20




በሀድያና ሥልጤ ሀገረ ስብከት ውስጥ ቤተክርስቲያኗ በኢ-አማንያን ተቃጥሎባቸው ሳይሰራ በመቆየቱ ምክንያት “ክርስትናችንን አንክድም፤ ማህተባችንን አንበጥስም” በማለት ከ32 ዓመታት በላይ በዛፍ ስር በመሰባሰብ እና ስዕለ መድኃኔዓለም በማኖር ሥርዓት አምልኮ እየፈፀሙ ያሉትን ምዕመናን ወገኖቻችንን የተሟላ ሀይማኖታዊ እና መንፈሳዊ አምልኮተ እግዚአብሔር እንዲያገኙ እየተሰራ ያለውን የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ከፍፃሜ ለማድረስ በሀገረ ስብከቱ የበላይ ጠባቂ ሊቀ-ጳጳስ ፈቃድ ባገኘው ዕውቅና መሠረት የበኩላችንን ድጋፍ ለማድረግ የቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆች በተለይም የገጠር ቤተክርስቲያን ያለችበት ሁኔታ የሚያሳስበን ሁሉ በዚህ መንፈሣዊ በረከት በመሳተፍ በማህበሩ የባንክ አካውንት ቁጥር 1000017080249 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መርካቶ፤ ቦንብ ተራ ቅርንጫፍ ቤተክርስቲያኗን በመርዳት በተጨማሪም በየትኛውም ቦታ ያለን ምዕመናን ሁሉ በፀሎት፣ በጉልበት፣ ጥሬ ዕቃ በማቅረብ፣ የበኩላችንን እንድንወጣ መንፈሣዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡



ክብር ምስጋና ለመድኃኔዓለም ይሁን! ለፍፃሜ አድርሶ የበረከቱ ተካፋይ ለመሆን ያብቃን አሜን!!



ለተጨማሪ መረጃ፡    
   + 251911 14 36 53

       + 251911 24 90 37

       + 251911 53 41 97

       + 251910 01 60 08

Sunday, January 13, 2013

ጥር 6



ከጌታችን እየሱስ ከርስቶስ ዘጠኙ ንዑሳን በዓላት አንዱና የመጀመሪው ነው፤ ግዝረተ ክርስቶስ ይባላል፤ ሉቃ 1 ፡ 21   “ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ፥ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደ ተባለ፥ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ።  እመቤታችን ወደ ግዘረት ቤት ወሰደችው፤ ገራዡ ምላጩን ይዞ ቀረበ ነገር ግን ምላጩ እጁ ላይ ሳላ ውሃ ሆኖ ፈሰሰ፤ ጌታችንም በተአምራት የተገረዘ ሆኖ ተገኘ ይላል፤ ምነዋ ቢባል ጌታችን ደሙ የሚፈሰው ስጋውም  የሚቆረሰው አንዴ በእለተ ዐረብ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ጌታችን የሰውን ስርዓት ሁሉ ጠብቋል፤ እራሱ እንደተናገረው  እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። ማቴ 5 ፡ 17 አምላክ ነኝና እለቱን ተጸንሼ እለቱን ልወለድ አላለም 9 ወር ከ 5 ቀን ቆይቶ ተወለደ እንጂ እንደ ህጻናትም ዋይ ዋይ እያለም አለቀሰ፤ ደግሞም እየው በዛሬዋ ዕለትም ተገረዘ፤ የሚገርም ነው፡፡ መገረዝ ወይም አለመገረዝ ምንም አይጠቅምም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው፤ ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነበር በአማናዊው ጥምቀት ተተክቷል፡፡ እርሱ የጥበበኞች ፈጣሪ ሲሆን  ፊደል ሊቆጥር ወደ  ቄስ ትምህርት ቤት የኔታ መምህሩ ጋር ሄዷል፤ መምህሩ አሌፍ በል አለው ጌታም አሌፍ አለ፤ አሌፍ ማለት የዕብራይስጥ ሆሄ ነው እኛ ሀ ሁ ሂ ሃ … እንደምንለው እነሱ ደግሞ   አሌፍ ቤት ጋሜል  ዳሌጥ  ሄ  ዋው  ዛይ … ይላሉ፤ አናም ፊደል መቁጠር ጀመረ አሌፍ በል አለው አሌፍ አለ ቤት በል አለው መጀመሪያ የአሌፍን ትርጉም ንገረኝ እንጂ አለው መምህሩ ተናዶ እኔ የምልህን ዝም ብለክ በል አለው ጌታችንም መልሶ የአሌፍን ትርጉም ሳላውቅ ዘልዬ ቤት አልልም አለው ሂድ  ወላጅ ይዘህ ና አለው እመቤታችንን ይዞ ሄደ እኔ ልጅሽን ማስተማር አልችልም ይዘሽሊኝ ሂጂ አላት መምህሩ የአሌፍን ትርጉም ስለማያውቀው ነው፤ ሀ ማለት ሀለዎተ እግዚብሔር መሆኑን ስንቶች መምህራኖች ነግረውን ይሆን ለዚያም ነው እኮ “” ሀሌታዋ ሀ ”” የምንለው አጋ-ጣሚ ሆኖ ዛሬ የታላቁ አባት  የኖህ እረፍቱ ነው፤ “”ሐመሩ ሐ”” የምንለው ስያሜውን ያገኘው ከዚሁ ከኖህ መርከብ ነው፤ ሐመር ማለት መርከብ ማለትም አይደል፡ ይህም የእመቤታችን አንድም የቤተክርስቲያን ምሳሌ ነው፤ ጎበዝ መምህራን ፊደል ሲያስቆጥሩ ትርጉሙን ጭምር እየተናገሩ ታሪኩን እያነሱ እያወሱ ያስተምሩ ነበር፤ ያ መምህር ግን ትርጉሙን አያውቅም ነበርና ጌታን ወላጅ አምጣ አለው፤ ልጅሽን ማስተማር አልችልም ከአቅሜ በላይ ነው አለ፤ ሰፊ ታሪኩ ታምረ እየሱስ ላይ ይገኛል፡፡ ሌላው በዛሬዋ ቀን ቴስቢያዊው ነብዩ ኤልያስ በእሳት ሰረገላ ወደ ብሔረ ሕያዋን የተወሰደበት ቀን ነው፤ የዚህ ነብይ ልደቱ ታህሳስ 1 ቀን ነው፤  አዲስ አበባ አንጦጦ ራጉኤል ቤተክርስቲያን ታቦተ ህጉ አለ ዛሬ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፤ ከበዓሉ በረከት ያደሳትፈን፡፡   

                                ኤሊያስ በሰረገላ ወሰደው ደመና

                               ኤሊያስ ያረገው በእሳት ሰረገላ

                               በጾም በጸሎት ነው አይደለም በሌላ    

Wednesday, January 9, 2013

ጥር 1



እነሆ  የተባረከ ወርሃ ጥር ባተ፤ ይህ ወር ቀኑ 14 ሰዓት ሌሊቱ 10 ሰዓት ነው። በዚህ ወር ታላላቅ በዓላት ይከበራሉ ከነዚህም መካከል፤-  ብርሃነ ጥምቀቱ፤ ግዝረቱ፤ ቃና ዘገሊላ፤ ቅድስት ስላሴ፤ የእመቤታችን እረፍት፤የቅዱስ ጊዮርጊስ ዝርዎተ አጽሙ፤ የዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ፤የነብዩ ኤልያስ፤የቅዱስ ኡራኤል ዓመታዊ በዓላቸው ሲሆኑ ሌሎችም ታላላቅ ቅዱስን አባቶች ታስበውና ተዘክረው ይውላሉ። እነሆ ጥር 1 ቀን የቀዳሚ ሰማዕት የሊቀ ዲያቆናት የቅዱስ እስጢፋኖስ የእረፍት ቀኑ ነው፤ የዚህ ሰማዕት ልደቱም በዚሁ ቀን ነው። በስሙ በታነጹለት አብያተ ክርስቲያናት ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፤ ዝነኛው ገዳሙ ሃይቅ እስጢፋኖስ በመዲናችን አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የሚገኘው ደብሩ ከቀደምቶቹ አንዱ ነው። እስጢፋኖስ ማለት ወደብ ጸጥታ ማለት ሲሆን ቁጥሩ ከ 72ቱ አርድዕት ነው፤ ለምን ቀዳሚ ሰማዕት ተባለ ከሱ በፊት ሰማዕታት የሉም ነበርን ? ቢሉ መኖርስ አሉ የእርሱ ግን ቀዳሚ መባሉ ከጌታችን እርገት በኃላ ስለ ጌታችን መውረድ መወለድ መስክሮ የሞተ የመጀመሪያው እርሱ ስለሆነ ነው፤ እሺ ለምንስ ሊቀ ዲያቆናት ተባለ ቢሉ በሐዋርያት እጅ ከተሾሙት ሰባቱ ዲያቆናት ውስጥ የሁሉም አለቃ እርሱ ስለሆነ ነው ሐዋ 6 ፤ 5። መጽሐፍ ቅዱስ ስለእስጢፋኖስ እንዲህ ሲል በእውነት መሰከረ "እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበረ...ፊቱም የመልአክ ፊት ይመስል ነበር ፤  ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ  አልቻሉም ሐዋ 6፤ 8 ። እህሳ  አይሀድ አማጽያን መልስ መስጠት ቢያቅታቸው ድንጋይ አነሱ ልብ አናቱን እያሉ ወገሩት፤  ቀና ብሎ ቢመለከት ቅድስት ስላሴን አየ፤ አቤቱ ይህን ኃጢያት አትቁጠርባቸው ይቅር በላቸው እያለ  ነፍሱን ሰጠ። ሐዋ 7፤ 60፤

ቅዱስ እስጢፋኖስ የተወለደው በኢየሩሳሌም በምትገኝ ሐኖስ በተባለች ቦታ ነው:: አባቱ ስምዖን ሲባል እናቱ ደግሞ ሐና ትባላለች ነገዱ ከነገደ ብንያም ነው :: የኦሪትን ሕግና ሥርዓት ከኦሪቱ ምሁር ከገማልያል ተምሯል::በሐዋርያት ሥራ ምዕ. 6 እንደምናነበው ሕዝቡን በማዕድ ያገለግሉ ዘንድ ሰባት ዲያቆናት ተመርጠዋል ከእነዚህ መካከል ቅዱስ እስጢፋኖስ አንዱ ሲሆን ለስድስቱ ዲያቆናት ደግሞ አለቃ( ሊቀ ዲያቆን) ሆኖ ተሹሟል ይህም የሆነው በጥቅምት 17 ነው ::
ቅዱስ እስጢፋኖስ በማዕድ አገልግሎት ሕዝቡን ከማገልገሉ በተጨማሪ ወንጌልን ይሰብክ ነበር ተአምራትን የማድረግ ጸጋም ተሰጥቶት ነበር በዚህም አገልግሎቱ ብዙዎችን ወደክርስትና መልሷል:: በዚህም አይሁድ በቅናት ተነሳስተው በሐሰት ከሰሱት ከከተማውም ወደ ውጭ አውጥተው ቄዳር በተባለ ቦታ በድንጋይ ወገሩት በሚወግሩትም ጊዜ ሰማያት ተከፍተው ምሥጢረ ሥላሴን (እግዚአብሔርን በሦስትነቱ ) ተመለከተ ኢየሱስ ክርስቶስንም በአብ ቀኝ ተቀምጦ አየ ለሚወግሩትም ሰዎች ከአምላኩ እንዲህ በማለት ምሕረትን ለመነ "ጌታ ሆይ ይህንን ኃጢአት አትቁጠርባቸው "በመጨረሻም "ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል" ብሎ ነፍሱን ሰጠ ::የሐዋርያት ሥራ ምዕ 7
በተወለደ በ 30 ዓመቱ በ35 ዓ.ም በሰማዕትነት ዐረፈ::

ከሰማዕቱ በረከት ያሳትፈን።  

Tuesday, December 25, 2012

ላፍቶ ሌንቃ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ሁኔታ



ላፍቶ ሌንቃ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ሁኔታ በአጭሩ


ቦታው ከአ.አ 210 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከምትገኘዋ ላፍቶ ሌንቃ የምትባል የገጠር ከተማ ሲደርሱ ወደ ቀኝ የሚገነጠለውን እና ወደ ስልጤ ዞን እና ቄልጦ ከተማ የሚወስደውን ኮረኮንቻማ የገጠር መንገድ ይዘው ሲጓዙ በግምት ከ4-5 ኪ.ሜ በኋላ ያገኙታል፡፡ ታሪክ ቤተክርስቲያኑ የተመሰረተበትን ዘመን በእርግጠኝነት ለማወቅ እና እና ለመናገር የሚያስችል በቂ መረጃ የሌለ ቢሆንም በጣም ብዙ የሆኑ ዘመናትን እንዳስቆጠረ የሀገር ሽማግሌዎች የተናገሩ እና በአካባቢው ላይ ያሉ የጥንት አባቶች ሲጠቀሙበት የነበሩ ዋሻዎች በውስጣቸውም የተገኘው የመስቀል ምልክት እና ፅሁፍ ምስክር ሲሆኑ በይበልጥ ግን ጥናት እና ምርምር ሊደረግበት የሚገባው ነገር ነው፡፡ ተጨባጭ ሁኔታ ይህ ቤተክርስቲያን አሁን ያለበት ሁኔታ እስከ ዛሬ ካየነው ከሠማነው ሁሉ የሚለይ እና እጅግ የሚያሳዝን ሁኔታ ነው፡፡ ሌሎች ቦታዎች ቢያንስ የሚያፈሱ ያረጁ በመቃብር ቤት ያሉ…. ብቻ የሆነ ትንሽ ነገር ያላቸው ናቸው፡፡ እዚህ ግን ምንም የለም እንደ ቤተክርስቲያን የሚያገለግለው ዋርካ/ዛፍ/ ሲሆን ከስሩ ስዕለ መድኃኔዓለምን በማስቀመጥ ይጠቀሙበታል፡፡ በፊት የነበረው ቤተክርስቲያን በተለያየ ጊዜ የተነሱ አፅራረ ቤተክርስቲያን ለ 3 ጊዜ ያፈረሱት ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ በ1971 ዓ.ም ከዛሬ 32 ዓመታት በፊት በአህዛብ የተቃጠለ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ ለዚህን ያህል ዓመታት ሙሉ በአካባቢው ያሉት 7ዐ ክርስቲያኖች ቤተክርስቲያን አግኝተው/አይተው/አያውቁም ነገር ግን ሃይማኖታችንን አንክድም ማተባችንን አንበጥስም በማለት ያለ መምህር በመፅናት ለብዙዎች አርአያ ለመሆን የሚችሉ ዕንቊ የቤተክርስቲያን ልጆች ያሉበት ቦታ ነው፡፡ እነዚህ ምእመናን ለ 32 ዓመታት ያሳለፉትን ጭንቅ /መከራ/ ተናግሮ መጨረስ የማይቻል በሰው አእምሮ የማይገመት አሰቃቂ ለመግለፅም የሚከብድ ነው፡፡ የቤተክርስቲያኑን ይዞታ አንሰጥም በማለታቸው ምክንያት ከ4 ጊዜ በላይ ታስረዋል ተገርፈዋል መከራም ደርሶባቸዋል፡፡ ልጅ ወልደው ክርስትና ማስነሳት ንስሀ መግባት ማስቀደስ…. የማይታሰቡ ነገሮች ናቸው፡፡ ሰው ሲሞት እንኳ ጸሎተ ፍትሀት ሳይደረግለት ዝም ብለው ቤተክርስቲያኑ የተቃጠለበት ቦታ አምጥተው ይቀብሩታል፡፡ አስከ አሁንም ድረስ የልጅነት ጥምቀት ያልተጠመቁ ህፃናት እና ወጣቶች ያሉ ሲሆን አንገታቸው ላይ ማህተብ በማሰር እኔ ክርስቲያን ነኝ በማለት በአህዛብ መካከል ይመሰክራሉ፡፡ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ በእለተ ሰንበት ተኝቶ አያረፍድም ወንዱም ሴቱም ህፃናቱም ትልልቆቹም ነጠላቸውን አጣፍተው ጋቢያቸውን አደግድገው ቤተክርስቲያኑ የተቃጠለበት ቦታ የምትገኝ አንድ ዛፍ ስር የመድኃኔዓለምን ስዕል በማኖር/በማስቀመጥ/ ይሰግዳሉ ይማፀናሉ፣ይለምናሉ ሥርዓተ አምልኮታቸውንም ይፈፅማሉ፡፡ ወር በገባ በ27 የመድኃኔዓለም ዕለት ተራ ይዘው ዳቦ በመጋገር ጠላ በመጥመቅ / ጠበል ፀዲቅ በማዘጋጀት/ መድኃኔዓለምን ይዘክራሉ፡፡ በአጠቃላይ በአህዛብ ተከበው ሃይማኖትን በማፅናት አስደናቂ ተጋድሎ በመፈፀም ላይ ይገኛሉ፡፡



ተአምራት፡- በቦታው ላይ የተገለጡት ብዙ ተአምራት ቢሆኑም ለጊዜው ጥቂቶቹ



 1. ቤተክርስቲያኑን ያቃጠሉት 2 ወንድ እና 1 ሴት አህዛብ ሲሆኑ፡- ሴቲቱ እሳት በእንስራ ደብቃ ይዛ በመምጣት ቤተክርስቲያኑ በር ላይ ይጠብgት ለነበሩ 2ቱ ወንዶች በመስጠት ተባብረው ካቃጠሉት በኋላ በተለያየ ወር የመድኃኔዓለም እለት 2ቱም ወንዶች በመብረቅ የተቀጡ /የሞቱ/ መሆናቸው፡፡ሴቲቱም ከብቶችዋ በሙሉ በመብረቅ ማለቃቸው፤



2. ቤተክርስቲያኑ ሲቃጠል የነበሩ አገልጋይ መልሶ ለማሰራት የተሰበሰበውን ብዙ ገንዘብ በእጃቸው አድርገው ከአገልጋያቸው ጭምር ወደ እስልምና በገቡ በእለቱ አይነስውር መሆናቸው አገልጋዩም ሽባ መሆኑ እና እስከዛሬ በህይወት መኖራቸው፤



3. ቤተክርስቲያኑ በተቃጠለበት ቦታ እና አፀዶች መካከል ዝማሬ ቃጭልና እና ከበሮ የሚሰማ ዕጣን /ማዕጠንት/ የሚሸት መሆኑ



4. ጥንታውያን ዋሻዎች /ሰው የሚገባባቸው እና የማይገባባቸው/ሲኖሩ በድፍረት የገቡት አንደበተ-ዲዳ፤ዓይነ-ስውር መሆን እና በእሳት እየተቃጠሉ መውጣት በተጨማሪም ዝማሬ ቅዳሴ ወዘተ በዋሻዎቹ ውስጥ መሰማት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ በተጨማሪም በተለያዩ ቅዱሳት/ቅዱሳን/ ስም የተሰየሙ ፍል/ሙቅ/ጠበሎች ያሉ ሲሆን ህዝብም አህዛብም እየተጠቀሙባቸው በመፈወስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ቀጣይ ተግባር፡- በሀዲያ እና ስልጢ ሀገረ ስብከት ውስጥ ያሉትን ችግሮች እና በምእመናኑም ላይ የሚደርሰውን መከራ እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ለማስወገድ በማሰብ የቤተክርስቲያን ልጆች በመሰባሰብ እና በመምከር ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመነጋገር አብሮ በመስራት እና እውቅና በመውሰድ በመጀመሪያ ደረጃ የላፍቶ ሌንቃ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያንን በተገቢው ሁኔታ እና በአጭር ጊዜ ለማቋቋም፤ በቀጣይነት ደግሞ ሀገረ ስብከቱን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ ያሉትን ችግሮች ለዘለቄታው ለመቅረፍ እና ለማስወገድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሀዲያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት ቅዱስ እንጦንስ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር” ማኅበር ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም የቤተክርስቲያን ነገር የሚያሳስበው አካል ማኅበራትም ሆኑ ምእመናን ከዚህ የባሰ ሁኔታ ስለሌለ በኅብረት ሆነን አስቸኳይ እና ዘለቄታዊ መፍትሄ እንድንሰጥ ሁላችንም የምንችለውን ሁሉ እና የሚጠበቅብንን እንድናደርግ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡  50 ሎሚ ለ1 ሰው ሸክሙ ነው ለ50 ሰዎች ግን ጌጥ ነው እንርዳዳ ይህችን ቤተክርስትያን እንጨርስ ከእግዚያአብሔር ጋራ

 

ህንፃ ቤተክርስቲያኑ እየተሰራ ሲሆን የቤተ ክርስቲያኑን ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በተቸላችሁ መርዳት ይቻላል..ኑ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንስራ መ.ነህ 2:20… ቅዱስ እንጦንስ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር  Commercial Bank of Ethiopia, Bomb Tera Branch. Account no. 1000017080249 mobile +251911143653, +251911780816, +251910016008 ክብር ምስጋና ለመድሓኔአለም ይሁን፡፡ለፍፃሜው አድርሶ የበረከቱ ተካፋይ ለመሆን ያብቃን፡፡በርቱ እመቤቴ ከነልጅዋ ትርዳችሁ ትርዳን፡፡


ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!