Sunday, March 17, 2013

የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት (ዘወረደ)

ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ /መዝ 2፡11-12/

የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት (ዘወረደ) ለአጠቃላይ ጾሙ መግቢያ የሚሆኑ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ትምህርቶች(መልዕክቶች) ይተላለፉበታል። እነዚህን ቀጥለን እንመለከታለን።

1.         ስለ ጾም

ዘወረደ የታላቁ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን የጾም አዋጅ ታውጅበታለች፤ ስለ ጾም ጥቅምና እንዴት መጾም እንዳለብን ታስተምረናለች፡፡ጾመ ድጓው አከለክሙ መዋእል ዘኃለፈ ዘተቀነይክሙ ለግእዘ ሥጋክሙ፤ ለሥጋቸሁ ፈቃድ የተገዛችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋል፤ ከአሁን በኋላ ግን ጹሙ፣ ጸልዩ ለእግዚአብሔር ተገዙ እያለ የጾም አዋጅ ያውጃል።
ጾም ፈቃደ ስጋን ለፈቃደ ነፍስ፣ ፈቃደ ነፍስን ለፈቃደ እግዚአብሔር/ለመንፈስ ቅዱስ/ የምናስገዛበት መንፈሳዊ መሳሪያ ነው፡፡ጾሙ ይህ የሚደረግበት መሆኑን ቤተክርስቲያን ሳምንቱ በሚጀመርበት ሰንበት በሚሰበከው ምስባክ እንዲህ ብላ ታሳስባለች፤ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፣በረዓድም ደስ ይበላችሁ /መዝ 2፡11-12/ ጾም ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከሌሎች ምቾቶችና ደስታዎች ከመከልከል ያለፈ ጥልቅ ትርጉም ያለው ተግባር ነው። ጾም ውጤታማ እንዲሆን እነዚህ መከልከሎች ከጸሎት ፣ ከፍቅርና ራስን ከማዋረድ ጋር መተባበር አለባቸውና በዚህ ሳምንት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ እያለች ታስተምራለች፦ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ ከመ ያብርህ ብርሃነ ስብሃቲሁ በላዕሌነ፤ (የእግዚአብሔር) የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም ፤ወንድማችንንም እንውደድ
(ጾመ ድጓ)።በዘወረደ እሁድ የሚነበቡት ምንባባትም ይህንን መልዕክት የያዙ ናቸው።ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡ እግዚአብሔርን ቅረቡት፤ ይቀርባችሁማል፤ እናንተ ኃጥኣን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት ዐሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ፡፡ እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ÷ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል፡፡ /ያዕ 4÷6-10/
 “ በውኑ እንግዲህ በስሙ እናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? ነገር ግን ለድሆች መራራትን÷ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና፡፡ /ዕብ 13÷15-16/
“ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና ። /ዕብ. 13፥9/በጾም የተጠቀሙ ቅዱሳንን እያሰብን ለጾም እንድንተጋም ወደ እነርሱ እንድንመለከት ቤተክርስቲያን ትጠቁማለች፡፡ ሳምንቱ በሚጀምርበት ሳምንት የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክትእንዲህ ይላል፡፡
“የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው። /ዕብ. 13፥7/ጾመ ድጓው ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹን እንዲህ እያለ ያስታውሰናል፤የእግዚአብሔር የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም፤ ወንድሞቻችንም እንውደድ፤ ኤልያስ በጾም ወደ ሰማይ አርጓልና፤ዳንኤልም ከአናብስት አፍ ድኗልና፡፡



2.         ስለ እግዚአብሔር ወልድ መውረድ (ሥጋዌ)

ከዐቢይ ጾም ጀምሮ እስከ ጰራቅሊጦስ ድረስ ያሉት ዕለታት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን ያደረጋቸው ነገሮች (ማስተማሩ፣ ተአምራት ማድረጉ፣ በፈቃዱ ተላልፎ መሰጠቱ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱ፣ መንፈስ ቅዱስን መላኩ) በስፋት የሚነገርባቸው ናቸው።
የእነዚህ ሁሉ ነገሮች መሠረትና ያገኘናቸው ጸጋዎች ሁሉ ምንጭ የእግዚአብሔር ወልድ መውረድ (ሰው መሆን) ነው።ይህ ሣምንት የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሣምንት እንደመሆኑ ቀጥለው ለሚነገሩት ነገሮች መሠረት የሆነው ይህ የእግዚአብሔር መውረድ ይነገርበታል። ዘወረደ (የወረደው) የሚል ስያሜ የተሰጠውም ከዚህ በመነሳት ነው።
ሣምንቱ በሚጀመርበት ሰንበት የሚነበበው ወንጌል ይህን መልእክት የሚያስተላልፍ ነው።እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ነገር ግን ምስክርነታችንንም አትቀበሉትም። በምድር ያለውን ስነግራችሁ ካላመናችሁኝ፥ በሰማይ  ያለውን ብነግራችሁ እንዴት ታምኑኛላችሁ? ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ  በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው። ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው፡፡ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዳይጠፋ።በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶታልና። /ዮሐ. 3፥11-16/ጾመ ድጓው የሚጀምረውም እንዲህ በማለት ነው፣ ዘወረደ እምላዕሉ፣ አይሁድ ሰቀሉ. እግዚአ ኩሉ ዘየሀዩ በቃሉ፤ .በቃሉ የሚያድነውን ከላይ የወረደውን የሁሉን ጌታ አይሁድ ሰቀሉት

3.         ስለ ትምህርት

 ዐቢይ ጾም የትምህርት ዘመን ነው። በጥንት ቤተ ክርስቲያን አዳዲስ አማንያን /ንዑሰ ክርስቲያን/ የሚጠመቁት በትንሣኤ በዓል ስለነበር በዐቢይ ጾም ሰፊ ትምህርት ይሰጣቸው ነበር።ዛሬም ዐቢይ ጾም ጌታችን በዚህ ምድር በእግረ ሥጋ በተመላለሰባቸው ዘመናት ያደረጋቸው  ነገሮች (ትምህርቱ፣ ተአምራቱ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤው ) በሣምንታት ተከፋፍለውና ተደራጅተው የምንማርበት የትምህርት ዘመን ነው። በአብነት ትምህርት ቤቶቻችንም ዐቢይ ጾም ዋነኛ የትምህርት ዘመን መሆኑ ይታወቃል።
ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን የትምህርት ዘመን በሆነው ዐቢይ ጾም መግቢያ ላይ ስለ ትምህርትና ስለ መምህራን እንዲህ እያለች ትሰብካለች፤
“የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም የሚኖር እርሱ ነውና። ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ። /ዕብ. 13፥7-9/
“ለመምህሮቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም፤ስለ እናንተ በእግዚአብሔር ፊት ምላሽ የሚሰጡ እንደመሆናቸው፣ ይህን ሳያዝኑ ደስ ብሎአቸው ያደርጉት ዘንድ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉና፡፡ /ዕብ. 13፥17/
አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ መዋዕለ ጾሙን በሠላም አሳልፈህ የትንሣኤህን ብርሃን ለማየት እንድታበቃን እንለምንሃለን። አሜን።

በዲ/ን አሉላ መብራቱ

Thursday, March 7, 2013

ዐቢይ ጾም

ጾም ማለት ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ ፍት.አን.15 “ጾምሰ ተከልኦተ ብዕሊ ዕምመብልዕ በጊዜ እውቅ” ጾም ማለት በታወቀው ዕለት በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡ መብል መጠጥ የኀጢአት መሠረት ነው በመብል ምክንያት ሞት በሰው ልጆች ላይ መጣ “ይችን ዕፀ በለስ ብትበሉ ሞትን ትሞታላችሁ” ዘፍ.2፥17 ጾም ማለት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል ወይም ለሰውነት የሚያምረውን የሚያስጐመዥውን ነገር መተው ማለት ነው፡፡
መብል መጠጥ ከልክ ሲያልፍ ከተዘወተረም ከእግዚአብሔር ይለያል፤ “ያዕቆብ በላ ጠገበ ወፈረ ገዘፈ ደነደነ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ተወ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር ተለየ” ዘዳ.32፥15-17 “የእግዚአብሔር መንግሥት መብልና መጠጥን አትሰብክም” ሮሜ.14፥16፣ 1ቆሮ.8፥8-13 “ዛሬ የሚራቡ የሚጠሙ ብፁአን ናቸው ይጠግባሉና ማቴ.5፥6 ጾም የሥጋ መቅጫ ነው፤ “ነፍሴን /ሰውነቴን/ በጾም ቀጣኋት መዝ.68፥10 ጾም በነቢያት የተመሠረተ በክርስቶስ የጸና በሐዋርያትም የተሰበከና የተረጋገጠ ለክርስቲያኖች ዲያብሎስን ድል የምንነሣበት መንፈሳዊ የጦር ዕቃ ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምረን ይህን ጾም ከምግብ ለመከልከል ጋር ጸሎትን፥ ስግደትን፥ ምጽዋትንና የንስሐ ዕንባን ጨምረን እንጹመው፡፡ ጌታችንና ነቢያት፣ ሐዋርያት የተውልን መንፈሳዊ መሣሪያ ነውና፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጾም የጾመው ለአብነት፣ ለማስተማር፣ ለአርዓያ ነው፡፡ በዚህ ታላቅ ጾም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ፣ ከሰው የሥጋ ጠባይ የሚመጣ ስስትና ፍቅረ ንዋይ ድል የተነሱበት ነው፡፡ እኛም ይህን እያሰብን በተለያየ መንገድ የሚመጣብንን ፈተና ለማራቅ ከዚህ ታላቅ ጾም በረከት እንድናገኝ እንጾማለን፡፡ ጸልዮ ጸልዩ፣ ጾሞ ጹሙ ብሎናል፡፡ ማቴ.6-16፡፡ ስለዚህም ትእዛዙን ለማክበር እንጾማለን፡፡
 የዚህ ታላቅ ጾም ስያሜዎች፡-
 1. ዐቢይ ጾም
 የባሕርይ አምላክ በሆነዉ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተ በመሆኑ ዐቢይ ወይም ታላቅ ጾም ይባላል፡፡
  2. ጾመ ሁዳዴ
 በጥንት ጊዜ ገባሮች ለባለ ርስት የሚያርሱት መሬት ሁዳዴ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ እኛም ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰብን የምንጾመው በመሆኑ ጾመ ሁዳዴ ተብሏል፡፡
 3. የካሳ ጾም
 አዳምና ሔዋን ከገነት የተባረሩት ለውርደት ሞት ለሲዖል ባርነት የበቁት በመብል ምክንያት ነው፡፡ በመብል ምክንያት የሞተውን የሰው ልጅ ጌታችን በፈቃዱ በፈጸመው ጾም ካሰው፤ መንፈሳዊ ረሃብን በረሃቡ ካሰለት፡፡ ስለዚህም የካሳ ጾም ተባለ፡፡
 4. የድል ጾም
 አርዕስተ ኃጣውእ /ማቴ. 4/ ድል የተነሱበት በመሆኑ የድል ጾም ተብሏል፡፡
5. የመሸጋገሪያ ጾም
 ጌታችን ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ወንጌል ሊያሸጋግረን የጾመው ጾም በመሆኑ የመሸጋገሪያ ጾም ተብሏል፡፡

  6. ጾመ አስተምህሮ
 ጌታችን የጾመው ለትምህርት ነው፡፡ እርሱ መጾም ያለበት ሆኖ አይደለም፡፡ ስለዚህም ይህ ጾም ጾመ አስተምህሮ ይባላል፡፡  አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ ማቴ.4፥2     
 7. የቀድሶተ ገዳም ጾም
 ጌታችን ከከተማ ርቆ ከሰው ተለይቶ በመጾም ከከተማ ርቆ ከሰው ተለይቶ በብሕትውና መኖርን ቀድሶ የሰጠበት፣ የመጥምቁ ዮሐንስና የነቢዩ ኤልያስን ገዳማዊነት የባረከበት በመሆኑ የቀድሶተ ገዳም ጾም ተብሏል፡፡
 8. የመዘጋጃ ጾም
 ሕዝበ እሥራኤል የፋሲካውን በግ ከመመገባቸው በፊት ዝግጅት ያደርጉ ነበር፡፡ እኛም ትንሣኤን ከማክበራችን፣ ሥጋና ደሙን ከመቀበላችን በፊት በጾምና በጸሎት ዝግጅት የምናደርግበት በመሆኑ የመዘጋጃ ጾም ተብሏል፡፡
 ዓቢይ ጾም ስምንት ሳምንት ማለትም 55 ቀናት አሉት፡፡ ከእነዚህም ቀናት ውሰጥ ሰባት ቅዳሜና ስምንት እሑዶች ይገኛሉ፡፡ አሥራ አምስት ቀናት ማለት ነው፡፡ እነዚህ ከጥሉላት እንጂ ከእህል ውኃ ስለማይጾሙ የሙሉ ቀናት ጾም አርባ ቀናት ብቻ ናቸዉ፡
የመጀመሪያው ሳምንት «ዘወረደ» ማለት በቀጥታ፣ ቃል በቃል ሲተረጐም «የወረደ» ማለት ነው፡፡ ይህም በምስጢሩ አምላክ ወልደ አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም በቅዱስ ፈቃዱ ሰው ሆኖ ከሰማየ ሰማያት  ከባሕርይ ልዕልናው በትሕትና ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመላክት፣ ይህም የሚታወስበት፣ የሚወሳበት የዐቢይ ጾም አንደኛው ሳምንት ነው፡፡ ዮሐ.313፡፡ በጾምነቱ ግን ለዐቢይ ጾም መግቢያ ሆኖ ታላቅ ገድልና ድል የተገኘበት ጾመ «ሕርቃል» ተብሎ ይጠራል፡፡ ሕርቃል 614 . የቢዛንታይን ንጉሥ ነበር፡፡ ይህ ሳምንት በስሙ የተጠራበትም ምክንያት በዘመኑ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር፡፡ ምእመናን «ተዋግተህ አስመልስልን» አሉት፡፡ እርሱም «ሐዋርያት ነፍስ የገደለ መላ ዘመኑን ይጹም ብለዋል፡፡ ስለዚህ ይኽንን የዕድሜ ልክ ጾም ፈርቼ እንጂ ደስ ይለኛል» ሲል መለሰላቸው፡፡ እነርሱም «የአንድ ሰው ዕድሜ ቢኖር ሰባ ሰማኒያ ዘመን ነው፡፡ እኛ ተካፍለን እንጾምልሃለን» ስላሉት ፋርስ ዘምቶ መስቀሉን ከእነዚያ ነጥቆ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል፡፡ መታሰቢያም እንዲሆን ይህን የጾም ሳምንት በቀኖና ውስጥ አስገቡት፡፡ የመጀመሪያው ሳምንት ጾሙም ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ታሪኩ የመስቀል ፍቅር የተገለጠበት ታሪክ ነው፡፡

መዋዕለ ጾሙን በሰላመ ያስፈጽመን


Friday, February 22, 2013

ታላቅ መንፈሳዊ ጉዞ!!!!!!!!!!!!!!

ታላቅ መንፈሳዊ ጉዞ!!!!!!!!!!!!!!
ወደ ላፍቶ ሌንቃ መድኃኔዓለም (እሁድ መጋቢት 22 2005) ደርሶ መልስ

እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እሁድ መጋቢት 22 2005) . ወደ ላፍቶ ሌንቃ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ደርሶ መልስ መንፈሳዊ ጉዞ ለመሄድ አስበናል፡፡ ቤተክርስቲያኑ ከአ. 210 . ርቀት ላይ ከምትገኘዋ ላፍቶ ሌንቃ የምትባል የገጠር ከተማ ሲደርሱ ወደ ቀኝ የሚገነጠለውን እና ወደ ስልጤ ዞን እና ቄልጦ ከተማ የሚወስደውን ኮረኮንቻማ የገጠር መንገድ ይዘው ሲጓዙ በግምት 4-5 . በኋላ የሚገኝ ሲሆን ''ሃይማኖታችንን አንክድም ማህተባችንን አንበጥስም'' በማለት በዋርካ ስር የአምላካችንን የመድኃኔዓለምን ምስለ ፍቁር በማድረግ አምላካቸውን ሲያመሰግኑ እዚህ ደርሰዋል እርስዎም በዚህ መንፈሳዊ ጉዞ ላይ እንዲሳተፉ መንፈሣዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ትኬቱን ከፈለጉ ትኬቱ ላይ ባለው ስልክ ያገኙናል፡፡
ticketun lemagegnt bezih silek yedwelu /0911534197 /0911803435/0911921830/0910016008