Saturday, November 17, 2012

ቅዱስ እንጦንስ

የበረሃዉ መልአክ ቅዱስ እንጦንስ
በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ




እንደተለመደው የኦሪት ዘፍጥረትን ትርጓሜ መሠረት ያደረገውን ተከታታይ ትምህርት ለመማር በማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ ውስጥ ካሉት አዳራሾች በአንዱ ተሰብስበናል፡፡ ትምህርቱ ከመጀመሩ በፊት በወረቀት ለሚጠየቁት ጥያቄዎች የሚሰጡት መልሶች ሁላችንም ስለሚያጓጓን በመጠባበቅ ተቀምጠናል። ከመምህራችን የቀረበው የዕለቱ ጥያቄ ግን ሌላ ነበር። «ዛሬ ቀኑ ስንት ነውየሚል፡፡ ጥር 22 በማለት መለስን፡፡ «ዛሬ የዕለቱ መታሰቢያነት ለማን ነውቀጥሎ ጠየቀን፡፡ መቼም ቅዱስ ዑራኤል መሆኑን አያጣውም፣ ግን ለምን ጠየቀን? በአእምሮዬ የሚመላለስ ጥያቄ ነበር፡፡ ለነገሩ ዕለቱ የተለየ ነገር ቢኖረው ነው እንጂ አይጠይቀንም ነበር፡፡ ይሄን እያሰብኩኝ ዝምታ በሰፈነበት፥ አንድ ልጅ እጁን አነሳና «የመልአኩ የቅዱስ ዑራኤል በዓል ነው» በማለት መለሰ፡፡ መምህራችንም ጥሩ ነው በማለት ተናገረና «ሌላስአለ በተረጋጋ አንደበት፡፡ ከዚህ በላይ እንኳን የማውቀው ነገር የለም አልኩኝ ለራሴ፡፡

 
ለማንኛውም በዚህ ዕለት ታላቁ አባት ርእሰ መነኮሳት ቅዱስ እንጦንስ ያረፈበት ዕለት ነው፡፡ ጽሌውም (የጽላት ነጥላ ቁጥር) በዋና ከተማችን አዲስ አበባ በምትገኘው መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ይገኛል፡፡ በርግጥ በራሱ ስም የተሰሩ ገዳማትም አሉ። ይህ የአዲስ አበባዉ ግን የእመቤታችን ጽሌ ከመምጣቱ በፊት በቅዱስ እንጦንስ ስም ይጠራ እንደ ነበር ሁሉ ተነገረን። ይሄንን ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን? የእኔ ጥያቄ ነበር። ለምን ለሌሎች አላካፍለውም

ቅዱስ እንጦንስ 25 . ቅማን/Qimn El-Arouse/ በሚባል በማዕከላዊ ግብጽ ነው የተወለደው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በቤተክርስቲያን ሳለ ወንጌል ሲነበብ ጌታችን ለባለፀጋው ጎልማሳ የነገረውን «ፍፁም ልትሆን ብትወድ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ሰጥተህ ተከተለኝ» የሚለውን የእግዚአብሔርን ጥሪ ስለሰማ ወላጆቹ ከታናሽ እህቱ ጋር ትተውለት የሞቱትን ሰፊና በመስኖ የሚለማ መሬት ቶሎ ሽጦ ለድሆች ከሰጠ በኋላ እህቱን ለደናግል ማኅበር አደራ ሰጥቶ የብሕትውና ኑሮውን ጀምሯል፡፡

ቅዱስ እንጦንስ በብዙ ተጋድሎና ፈተና በመካከለኛው የግብጽ በረሃ ውስጥ ብቻውን የኖረ ከዚያም ብዙ ተከታዮችን ያፈራ፣ የምንኩስና ሕይወትም ጀማሪ የሆነ አባት ነው፡፡
ቅዱስ እንጦንስ፣ የቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ወዳጁም ነበር፡፡ ርእሰ ባህታውያን የዋህ ጳውሊንም ከፍኖ የቀበረው ቅዱስ አትናቴዎስ በሰጠው ካባ ሲሆን በመልሱም ለቅዱስ አትናቴዎስ የቅዱስ ጳውሊን ለራሱ ከዘንባባ የሠራውን እንደታታ ቅርጫት የመሰለውን ዐፅፍ ልብስ ሰጥቶታል፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስም በበዓለ ትንሣኤና በበዓለ ሃምሣ በውስጥ ይለብሳት ነበር፡፡





በክርስቲያኖች ላይ መከራና ሞት በዓላውናን ነገሠታትና መኳንንት በታዘዘ ጊዜ ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ፍቅር እንደበግ እየተነዱ ወደሞት ይሔዱ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ እንጦንስ ከበአቱ ወጥቶ ወደ እስክንድርያ ሔደ÷ ተጠርተንም እንደሁ በእሽቅድምድም ለመሳተፍ አለበለዚያ ተሽቀዳዳሚዎችን ለመጎብኘት እንሒድ በማለት እንጦንዮስ ሰማዕትነትን ለመቀበል ከፍተኛ ጉጉት ነበረው፡፡ ነገር ግን እርሱን የብሕትውናና የምንኩስና ሕይወት አስተማሪ ይሆን ዘንድ ስለ ብዙዎች ጥቅም ጠበቀው፡፡ ሰማዕታት ለፍርድ ሲጠሩ አጅቦ ይሸኛቸዋል÷ እስኪገደሉም ድረስ አይለያቸውም፡፡ ዳኛው ድፍረቱንና የተከታዮቹን ብዛት ጽኑ መንፈሳቸውንም ባየ ጊዜ ማንም መነኩሴ ወደ ፍርድ ቤት አካባቢና በከተማው ውስጥ እንዳይታይ አዘዘ፡፡

እንጦንስ ግን ሰማዕታትን አጅቦ ከፍርድ ቤት ፊት ለፊት ዳኛው ሊያየው በሚችል ስፍራ ተገኘ። ሁሉም በመገኘቱ ሲደነቁ ኃላፊው በትሩን ይዞ ወደ እርሱ መጣ፥ እርሱ ግን የክርስቲያኖችን ጽኑ መንፈስ ያሳይ ዘንድ ምንም ሳይፈራ ቆመ።

ምንጭ፡ ያረጋል አበጋዝ (ዲ/ን) ና አሉላ ጥላሁን ፣ 1997። ነገረ ቅዱሳን 3። ማኅበረ ቅዱሳን፣ አ.አ።


የመነኮሳት ሕይወት
ምንም እንኳን የድንግልናና የምናኔ ኑሮ ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም የምንኩስና መሥራችና አባት ቅዱስ እንጦንስ ነው፡፡ አባ እንጦንስ ግብፅ ውስጥ በምትገኝ ቆማ በምትባል ቦታ በ251 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ወላጆቹ ሀብታሞችና ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከወላጆቹ ዕረፍት በኋላ የነበረውን ሀብት ለድሆች መጽውቶ መንኩሶ ብዙ ዓመት በብሕትውና ኖረ፡፡
በዚያን ጊዜ ብዙ ታምራትን ስለሠራ ሕዝቡ ግማሹ እሱን አይቶ ለማድነቅ የቀረው ደግሞ በእርሱ ጸሎት ለመፈወስ ወደነበረበት ቦታ ይጐርፍ ነበር፡፡ እርሱም በ356 ዓ.ም ዐረፈ፡፡

አባ ጳኩሚስ የተባለ ሌላው አባት በላይኛው ግብፅ ውስጥ ብዙ ገዳማትን በመሥራት የምንኩስናን ሕግና ሥርዓት በመወሰን ስለምንኩስና መስፋፋት ብዙ ደክሟል /290-347 ዓ.ም/፡፡ አንድ ቀን ወደ ዱር እንጨት ፍለጋ ሔዶ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጸለትና እንደ አባቶቻችን ሐዋርያት የአንድነትን ማኅበር ለመሥራት መነኮሳትን እንዲሰበስብ አዘዘው፡፡ ብዙ አማኞች እየናፈቁት ማግኘት ያልቻሉትን ገዳማዊ ሕይወት ያገኙ ዘንድ ገዳም ለመመሥረት የሚስችለውንና የሚያስተዳድርበትን በነሐስ ላይ የተቀረጸ ሕግ ሰጠው፡፡ አባ ጳኩሚስም ከመልአኩ በተሰጠው ሕግ መሠረት የሚተዳደር ገዳም አቋቋመ፡፡ ይኸውም መነኮሳቱ ጠዋትና ማታ አብረው እንዲፀልዩ በአንድነት እንዲሠሩ ገቢና ወጪያቸው አንድ ላይ እንዲሆን በአንድነት እንዲመገቡ፣ ልብሳቸው አንድ አይነት እንዲሆንና እነዚህን የመሳሰሉትን ደንቦች አወጣላቸው፡፡ በዚህ መሠረት መነኮሳቱ የዕለት ምግባቸውን የሚያገኙት እየሠሩ ነበር፡፡ ከሴቶችም የምንኩስናን ሕይወት የጀመረች የአባ ጳኩሚስ እህት ማርያም ናት፡፡

ከዚህ በኋላ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀምሮ ምንኩስና በግሪክ፣ በሮም፣ በሶሪያና በሌሎችም ሀገሮችም እየተስፋፋ ሄደ፡፡

የምንኩስናን ሕይወት ወደ ኢትዮጵያ ያመጡ በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በጉባዔ ኬልቄዶን /በሃይማኖት ስደት/ ምክንያት ከቁስጥንጥንያ፣ ከግብፅ፣ ከሶርያ፣ ከሮም፣ ከአንጾኪያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ዘጠኙ ቅዱሳን መነኮሳት ናቸው፡፡ ምንኩስና ከተመሠረተ ጀምሮ በየጊዜው ሕዝቡ ታላላቆችም ሳይቀሩ ወደ ገዳማቱ እየሄዱ ይመነኩሱ ነበር፡፡
ነገር ግን ከ9ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ በማኅበር ከሚኖሩት መነኮሳት መካከል ጥቂቶቹ ቀስ በቀስ ለብቻ በተለየ ቤት መኖር እያንዳንዱ መነኩሴ ለብቻ በፈለገበት ጊዜ መብላትና መተኛት ስለጀመረ በየገዳማቱ የመነኮሳቱ ኑሮ በማኅበር የሚኖሩትና ለብቻቸው የሚኖሩት ለሁለት ተከፈሉ፡፡

የድንግልና መሠረቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ስለ መንግሥተ ሰማያት ሰውነታቸውን ጃንደረባ ያደረጉ አሉና፤ መፈጸም የሚችል ግን ይፈጽም» ሲል የተናገረው የሕግ ቃል ነው፡፡ ማቴ. 19፡12
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
/ምንጭ፦ 'የዛሬዋ ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ' በዲ/ን አሐዱ አስረስ፣ ነሐሴ 1992 ዓ.ም/

No comments:

Post a Comment