Friday, December 7, 2012

ነገረ ማርያም በነገረ ድኅነት




 ቤተ ክርስቲያናችን ለምን ስለ እመቤታችን ዘወትር እንደምታስተምር አንዳንድ ሰዎች ግር ሲላቸው ይታያል፡፡ እንዲያውም ‹‹አላዋቂ ሳሚ...›› እንዲሉ ስለ እመቤታችን ማስተማር ስለ ጌታችን እንዳታስተምር አድርጓታል ብለው የሚናገሩም አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ግን ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምታስተምረው ለርሷ ካላት ልዩ ፍቅር ብቻ ወይም ስለጌታችን የምታስተምረው ለርሷ ካላት ልዩ ፍቅር ብቻ ወይም ስለጌታችን የምታስተምረው አልቆባት አይደለም፡፡  ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ሊቃውንት በላይ ለነገረ መለኰት ምሁርና ጥንቁቅ ከማግኘት የሰማይን ስፋት ልክ ማግኘቱ ሳይቀል አይቀርም፡፡
 በቅዳሴያችን፣ በዘወትር ጸሎታችን፣ በመዝሙራችን፣ በሥርዓታችን፣ በትውፊታችን፣ በአለባበሳችን ሳይቀር የነገረ ድኀነት ትምህርት የሌለበት የለም፡፡ ሰዎች ዐረፍተ ዘመናቸው ደርሶ ወደ መቃብር ሲሸኙ በምናደርግው ጸሎተ ፍትሐት ለክርስቲያኑ በሚደረገው የቀብር ሥነ ሥርዓት ሁሉ ነገረ ድኀነት ይሰበካል ይገለጣል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ነገረ ማርያምን ዘወትር ለምእመናን የምታስተምረው ከነገረ ድኀነት ጋር የተያያዘ ጥልቅ ምሥጢር ስላለው ነው፡፡ ነገረ ድኀነትን ለመማር፣ ለመረዳትና ለማመን ነገረ ማርያም መሠረትና መቅድም ነው፡፡ ያለ ነገረ ማርያም ነገረ ድኀነት፣ ያለመሠረት ቤት ማለት ነው፡፡ እስቲ ለዚህ ምስክር የሚሆኑ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፡፡

1. የሔዋን ካሣ
. እናታችን ሔዋን ምክንያተ ስህተት፣ ምክንያተ ሞት በመሆኗ ፍዳ መርገም ደርሶባት ነበር፡፡ ያበላችን ፍሬ ሞትን የሚያመጣ ከገነት የሚያስወጣ በመሆኑ ትውልድ ሁሉ ሲወቅሳት ይኖር ነበር፡፡

ዳግማዊት ሔዋን እመቤታችን ግን ምክንያተ ድኂን ሆነች፡፡ የሰጠችን ፍሬ ሞትን የሚያመጣ ሳይሆን ተበልቶ ተጠጥቶ የዘላለም ሕይወት የሚያሰጥ ነው /ዮሐ6&36/:: ትውልድ ሁሉ ሔዋንን ሲወቅስ ኖረ፡፡ እመቤታችንን ግን ትውልድ ሁሉ ያመሰግናታል /ሉቃ 1&48/:: ሶሪያዊው ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ ውዳሴው ‹‹ስለሔዋን የገነት በር ተዘጋ ዳግመኛም ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን፡፡ ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን›› ብሏል፡፡

. ሔዋን በዲያቢሎስ ተመክራ ኃጢአትን ጸነሰች፡፡ ሞትንም ወለደች፡፡ እመቤታችን ግን በሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ሕይወትን ፀነሰች ትንሣኤን ወለደች /ሉቃ 1&28-38/፡፡
በሴት የመጣ ሞት በሴት ድል ተመታ፡፡ ‹‹እመቤታችንን የሔዋን መድኃኒቷ›› ያሰኛትም ይኼው ነው፡፡ ይኼንን ድንቅ ምሥጢር ካልተረዳንና ካላመንን ሔዋን መካሥዋን፣ የሴቶች ክብራቸው መመለሱን በምን ተረድተን እንዴትስ ልናምን እንችላለን?

2. የአዳም ካሣ
. አዳም የተወለደው ከኀቱም ምድር ነው፡፡ ከአዳም በፊትም ሆነ በኋላ ሌላ ልጅ የላትም፡፡ አዳምን ያስገኘችው በጥበበ መንፈስ ቅዱስ በፈቃደ ሥላሴ እንጂ ዘር አላስፈለጋትም፡፡ በዚህ ግሩም ድንቅ ምሥጢር የተገኘ አዳም ግን ሞትን በራሱ ላይ በማምጣቱ ወደቀ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበትም አንዱና ዋነኛው ምክንያት ለቤዛ ዓለም፣ ለካሣ ዓለም ነው፡፡ ይኸንንም በመዋዕለ ይጋዌው በሠራው ሥራ ሁሉ ገልጦታል፡፡

ጌታችን ሲወለድ ያለወንድ ዘር፣ በግብረ መንፈስ ቅዱስ በኀቱም ድንግልና ከእመቤታችን ነው፡፡ የእመቤታችንን ድንግልና ካልተቀበልን የመጀመሪያው አዳም ከኋለኛው አዳም ይበልጣል ማለት ነው፡፡ ያነሰው ደግሞ የበለጠውን ሊያድን እንዴት ይቻለዋል? እኛስ እንዲህ አናምንም፡፡ ከኀትምት ምድር ተወልዶ የወደቀውን አዳም ያነሣው ዘንድ ያለወንድ ዘር ከድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ ምድር ከአዳም በፊትም ሆነ በኋላ ሌላ ልጅ እንዳላስገኘች እመቤታችንም ከጌታችን በፊትም ሆነ በኋላ በድንግልና ኖረች፡፡ በዚህም ዘላለማዊት ድንግል ትባላለች፡፡ ልበ አምላክ ዳዊት ይኼንን በምሳሌ ሲያስረዳን፡-
‹‹እውነት ከምድር በቀለች
ጸድቅና ሰላም ተስማሙ›› ብሏል (መዝ 84&1-11)፡፡ እውነት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው /ዮሐ14&7/፡፡ እውነት የበቀለባት ምድር ደግሞ እመቤታችን ናት፡፡ ጽድቅና ሰላም የተስማሙትም በልደተ ክርስቶስ ነው፡፡

. አዳም የተገኘው መርገም ካልደረሰባት ምድር ነው፡፡ ምድር መርገምን ያመጣችው በልጅዋ በአዳም በደል ነው፡፡ አምላክን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያምም በደል መርገም ያልደረሰባት ንጽሕት ቅድስት ናት፡፡ አስቀድማ በደል /ጥንተ አብሶ/ ነበረባት ካልን ከኋለኛው ምድር የቀደመችው ትበልጣለች ያሰኝብናል፡፡ ይኸ ከሆነ ደግሞ አዳም አዳም ተዋጀ፣ ተካሠ ወደ ክብሩ ተመለሰ ማለት አይቻልም፡፡ ያነሰው የበለጠውን ሊያከብረው አይችልምና፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን እመቤታችን የአዳም ኃጢአት ያልደረሰባት ናት ብላ የምታስተምረው ርቱዕ እንደሆነ በዚህ ይታወቃል፣ እምነቷ እንደ ሌሎቹ አይጣላምና፡፡ የሌሎቹ ግን የሚናገሩትም ሆነ የሚጽፉት እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው፡፡

አንዳንዶች እመቤታችን ‹‹ከአዳም ኃጢአት የነጻችው በብሥራተ ገብርኤል ነው›› ይላሉ፡፡ ይህ ከሆነማ የክርስቶስ መሞት ለከንቱ ሆነ ያሰኝባቸዋል፡፡ ብሥራተ መልአክ ከቀደመ ኃጢአት /ከጥንተ አብሶ / ነጻ የሚያወጣ ቢሆን ኖሮ በብሉይ እነ ብእሲተ ማኑሄ /መሳ 1&131-20/ በሐዲስ ደግሞ እነ ዘካርያስ /ሉቃ 1&13-20/ ከዚህ ቀንበር ነፃ በወጡ ነበር፡፡ በብሥራተ መልአክ ልጅ አግኝተዋልና፡፡ በሌላ በኩልም የመልአክ ብሥራት ከጥንተ አብሶ ለመላቀቅ ካስቻለ እልፍ አእላፍ መላእክት ተልከው አዳምን ከነዘሮቹ ባዳኑት ነበር፡፡ የቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ከጥንተ አብሶ ካላቀቀ ከክርስቶስ ሞት ጋር እኩል ነው ማለት ነው /ሎቱ ስብሐት/፡፡ እኛስ እንዲህ አንልም ይህ ከላይ ለመመልከት እንደሞከርነው የሃይማኖት ስሕተትን ያስከትላል፡፡

3. የሕያዋን እናት
አዳም ለሚስቱ የሕያዋን እናት ብሎ ስም አውጥቶ ነበር፡፡ ሔዋን ማለት የሕያዋን እናት ማለት ነውና /ዘፍ 3&2/፡፡ ነገር ግን የሕያዋን እናት በርግጥ አልነበረችም፡፡ እርስዋም ልጆችዋም የሞት ባሮች ነበሩና፡፡ ‹‹ከአዳም እስከ ሙሴ ሞት ነገሠ›› እንዲል (ሮሜ 5&19)፡፡ ታዲያ የሕያዋን እናት ማንናት?

የሰው ልጅ በጥፋቱ እናትም አባትም አጥቷል፡፡ አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን ከገነት ተባረሩ፡፡ ለኛ ቤዛ መከታ፣ አለኝታ ሊሆኑን ቀርቶ ለነርሱም አስፈልጓቸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአዳም ተገብቶ በሥጋ ብዕሲ መጣ፡፡ ወንዶቹ #እኛ ብቻ ተካስን የሔዋን ነገር ግን መና ቀረ$ እንዳይሉ እመቤታችንን መርጦና ቀድሶ አዘጋጀ፡፡ አባትም እናትም ያጣው የሰው ዘር አባት አገኘ፡፡ ‹‹አባ አባት ብለን የምንጠራበት የልጅነት ጸጋ ተሰጠን›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አባታችን ሆይ›› በሉ የተባልነውም ይኸ ክብር ስለተመለሰልን ነው (ሮሜ 8&15)፡፡ ስለሔዋን ደግሞ የሕያዋን እናት ትሆነን ዘንድ እመቤታችንን አገኘን፡፡ የሰው ልጅ ገነትንም እናቱንም ያጣው ባንድ ጊዜ እንደነበረው ሁሉ ገነትንም እናቱንም ያገኘው ደግሞ በአንድ ጊዜ ነው፡፡ እመቤታችን በጸሎታችን ብዛት፣ በቅድስናችን ብቃት ያገኘናት ሳትሆን ስለምታስፈልገን የተሰጠችን እናት ናት፡፡ ይህም ጌታችን በመልዕልተ መስቀል የሚወደውን ደቀመዝሙሩን ቅዱስ ዮሐንስን ‹‹እነኋት እናትህ›› ባለው ጊዜ ታውቋል /ዮሐ 19&19/፡፡ ነቢዩ ዳዊትም አስቀድሞ ‹‹ሰው እናታችን ጽዮን ይላል›› ሲል ተናግሮላት ነበር (መዝ 86&5)፡፡

አማናዊቷ ሔዋንም /እመሕያዋን/ እመቤታችን ናት፡፡ ልጇ ሞትን አሸንፎ እኛ ልጆቿ የምናሸንፍበትን ሥልጣን እንደሰጠን እርሷም ሞትን አሸንፋዋለችና እንዲህ እናምናለን እንዲህም እንመሰክራለን፡፡ ያለበለዚያ ግን የሰው ልጅ ወደ ጥንተ ክብሩ ተመለሰ ፍጹም ድኀነትን አገኘ ለማለት አንችልም፡፡

እንግዲህ በነዚህ ጥቂት ምሳሌዎች ነገረ ማርይም ለነገረ ድኀነት ምን ያህል መሠረት እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ነገረ ማርያምን በሚገባ ያልተረዳና ያልጠነቀቀ ነገረ ድኀነትንም ሆነ ነገረ መለኰትን ጠንቅቆ መረዳት አይቻለውም፡፡ አንድ ድንጋይ ከመሠረቱ ላይ በተነሣለት ቁጥር ቤቱም የዚያን ያህል እንደሚናጋ በነገረ ማርያም አንዳች ስህተት ብንጨምር የነገረ መለኰት ትምህርታችንም ሆነ እምነታችን የዚያኑ ያህል የተሳሳተ ይሆናል፡፡ ያለ ንጽሕት ሃይማኖት ደግሞ ንጽሕና አይገኝም፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ነገረ ማርያምን አዘውትራ የምታስተምረው ያለ ጥርጥርና ያለነቀፋም የምታምነው ለድኅነት መሠረት መሆኑን በተረዳ ነገር ስላወቀች ነው፡፡ በሥዕሎቻችን፣ በጸሎታችን፣ በመጻሕፍቶቻችን፣ በዝማሬዎቻችን፣ በሥርዓታችንና በትውፊታችንም ስለእመቤታችን የሚነሣው ለዚህ ነው፡፡ የቀረውን ደግሞ ሥላሴ ይግለጥልን፡፡ አሜን

Source: www.mahiberekidusan.org

No comments:

Post a Comment