የበረሃዉ መልአክ ቅዱስ እንጦንስ
በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
እንደተለመደው የኦሪት ዘፍጥረትን ትርጓሜ መሠረት ያደረገውን ተከታታይ ትምህርት ለመማር በማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ ውስጥ ካሉት አዳራሾች በአንዱ ተሰብስበናል፡፡ ትምህርቱ ከመጀመሩ በፊት በወረቀት ለሚጠየቁት ጥያቄዎች የሚሰጡት መልሶች ሁላችንም ስለሚያጓጓን በመጠባበቅ ተቀምጠናል። ከመምህራችን የቀረበው የዕለቱ ጥያቄ ግን ሌላ ነበር። «ዛሬ ቀኑ ስንት ነው?» የሚል፡፡ ጥር 22 በማለት መለስን፡፡ «ዛሬ የዕለቱ መታሰቢያነት ለማን ነው?» ቀጥሎ ጠየቀን፡፡ መቼም ቅዱስ ዑራኤል መሆኑን አያጣውም፣ ግን ለምን ጠየቀን? በአእምሮዬ የሚመላለስ ጥያቄ ነበር፡፡ ለነገሩ ዕለቱ የተለየ ነገር ቢኖረው ነው እንጂ አይጠይቀንም ነበር፡፡ ይሄን እያሰብኩኝ ዝምታ በሰፈነበት፥ አንድ ልጅ እጁን አነሳና «የመልአኩ የቅዱስ ዑራኤል በዓል ነው» በማለት መለሰ፡፡ መምህራችንም ጥሩ ነው በማለት ተናገረና «ሌላስ?» አለ በተረጋጋ አንደበት፡፡ ከዚህ በላይ እንኳን የማውቀው ነገር የለም አልኩኝ ለራሴ፡፡