Friday, April 26, 2013

ደብረ ዘይት

እንኳን ለጾመ እኩሌታው /ለደብረ ዘይት/ በሰላም አደረሳችሁ፡፡
ደብረ ዘይት

ብዙዎች በስሜ ይመጣሉ /ማቴ.24.1-36/


የዐቢይ ጾም አምስተኛው ሳምንት ደብረ ዘይት ይባላል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በደብረዘይት ነገረ ምጽአቱን እንዳስተማረ የሚነገርበት ሳምንት ነው፡፡ «ወእንዘ ይነብር እግዚእነ ውሰተ ደብረዘይት ቀርቡ ኀቤሁ አርዳኢሁ እንተበህቲቶም» ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ስምዖን፣ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ እንድርያስን ጨምሮ ቀርበው «ንገረን ይሄ መቼ ይሆናል?» በማለት ጥያቄ ጠየቁት፡፡ ጥያቄውም የዓለም መጨረሻውና የመምጫህ ምልክቱ ምንድን ነው? የሚል ነበር፡፡
ጌታችንም የዓለም መጨረሻውና ምልክቱን በዝርዝር አስረድቷቸዋል፡፡ እኛም ጊዜው ግድ ከሚለን አንፃር አጠር አድርገን ዋና ዋናዎችን እንመለከታን፡፡

- «ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ እኔ ክርሰቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎች ይስታሉ» የሚለው ኃይለ ቃለ የዓለምን መጨረሻ ከሚጠቁሙን ዋና ምልክቶች መካከል አንዱ የብዙዎች በስሙ መመጣት ነው፡፡ ይህም ከዚህ በፊት በዓለም ላይ ብዘዎች «እኔ ክርስቶስ ነኝ» ብለው የመጡ አሉ፡፡ ከዚህ በከፋ መልኩ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንኳ በየመንደሩ በክርስቶስ ስም የሚፈለፈሉ የእምነት መሳይ ድርጅቶች ዛሬ በሺዎች የሚቆጠሩ ሆነዋል፡፡ ስለዚህ ጌታችን በስሜ ይመጣሉ ማለቱ ለማስጠንቀቂያ በመሆኑ ሰዎች ተሰነካክለው እንዳይወድቁ ለማሳሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ስለ ሃይማኖት እውቀቱም ብቃቱም ሳይኖራቸው ክርሰቶስ በሕልም በራዕይ ተገለጠልኝ በማለት ሰይጣን የሚጫወትባቸው ብዘዎች ስለሆኑ ሌላው ማስተዋል አጥቶ እየተከተላቸው እንዳይስት ነው፡፡ ዛሬ ሰይጣናዊነት /Devilism/ እንኳ ክርስቶስን እንደመከተል የተቆጠረበት ጊዜ ነው፡፡

- «ጦርነም የጦርንም ወሬ ትሰማላችሁ» የኸም የአንድ ሀገር ሕዝብ ከሌላ የሀገር ሕዝብ፤ በአንድ ሀገር ውስጥ እርስ በርሱ በአንድ ቤተሰብ እንዲሁ መለያየትና መዋጋት በዓለም ይሰፍናል፡፡ የአንደኛውና የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ከዚያም በኃላ ያለው እልቂት የምጽአቱን ምልክት ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም የባሰ የእልቂት አይከሰትም ለማለት ምንም ማረጋገጫ የለንም ትንቢቱም የሚለው ይህ ጥቂት መሆኑንና ከዚህም የባሰ የትንቢት ማረጋገጫ መኖሩን ነው፡፡

- ወይም ራሀብ ቸነፍር የምድር መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፡፡ ይህም የሚያሳየው ከሀገራችን ጀምሮ ድሆች ሀገራትን ስንመለከት ረሀብ ይወራባቸዋል፡፡ የምድር መናወጥን ስናይ ለሁሉም ዓለም መኖሩን በየጊዜው የቴሌቨዥን መስኮቶች እያስረዱ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ ሌሎች የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ እልቂቶች በዓለማችን ላይ ሰፍነው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በአደጉ ሀገሮች ላይ የሚታየው የኑሮ ቀውስ ሁሉ የምጽአቱ መቃርብ ምልክት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን ይህ ገና የመጀመሪያው መከራ እንጂ ቀጣዩ ከዚህ የሚበልጥ መሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ ዋነኛው ደግሞ ሰዎች በረሀብ ነፍስ መምታታቸው ነው፡፡ ይህም ዓለም ዛሬ በሚዲያዎቹና በተለያየ መገናኛዎቹ እያደነቀ ያለው ዓለማዊነት በመሆኑ ዓለምን ወደ አንድ ባህል ለማሸጋገር /ግሎባለይዜሽን/ በሚል አሰተሳሰብ እግዚአብሔርን ማመን ትኩረት የማይሰጠው በመሆኑ አሁን ደግሞ መላው ዓለም እግዚአብሔርን እንዲዘነጋ እየተሠራ ነው፡፡ ዓለም ትኩረት የሚሰጠውና የሚያደንቀው ኳስ ተጫዎችን ፊልም ተዋናይን፣ ዘፋኝነትን ወዘተ መሆኑ ጊዜው መቅረቡን ያስረዳል፡፡

በመሆኑም ሰው ከቃለ እግዚአብሔር እጦት የተነሳ በረሀብ ነፍስ እየተጐዳ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህም በመጨረሻ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንድናጣና ገሀነመ እሳት እንድንወድቅ የሚያደርግ ነው፡፡

በተጨማሪም ስለኔ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፣ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኃል ፍቅር ትቀዘቅዛለች፣ ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው ወዘተ.. የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች ያዛሉ መልእክቶች አምላካችን አስተላልፉልናል ይህንንም በዝርዝር ብናይ በውስጣቸው ብዙ መልክቶች እናገኛለን፡፡ ዋናው ቁም ነገሩ ለምልክትነት የሚገለጸውን መከራና የክህደት ዜና ታግሶ በሃይማኖት መጽናት እጀግ ጠቃሚና ለመንግሥት ሰማያት የሚያበቃ ነው፡፡ የእግአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን፡፡ 

በአባ ዘሚካኤል

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment