Friday, December 7, 2012

፩. ነገረ ቅዱሳን /ክፍል አንድ/




 መግቢያ

፩፡፩  ነገር ማለት፡- በቁሙ ሲተረጐም ቃል ንባብ ወሬ የቃል ፍሬ ከድምጽ ጋር የሚስማማ በጽሕፈት በአንደበት የሚገለጥ ከልብና ከአፍ የሚወጣ በአንደበት የሚነገር ማለት ነው። ይኸውም መንገርን መስበክን ማስተማርን ማውራትን ማብሠርን ነገርን ሳያቋርጡ እንደ ውኃና ዝናም ማፍሰስን ማውረድን ማንጐድጐድን አሳብን ምሥጢርን በቃል መግለጥን በንባብ ማስጌጥን መልክ እያወጡ ምሳሌ እየሰጡ ማነጽና መቅረጽን የሚያመለክት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ « ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፡፡ » በማለት የዕብራውያን መልእክቱን የጀመረው ለዚህ ነው። ዕብ ፩፡፩ ግዕዙ « በብዙኅ ነገር » ይለዋል፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ሙሴን፦ «እግዚአብሔር አምላክ በስድስተኛው ቀን ፍጥረቱን ሁሉ ፈጥሮ እንደጨረሰ የፍጥረትን ነገር ሁሉ ጻፍ፤ » ብሎለታል፡፡ ግዕዙም የሚለው፦ « ጸሐፍ ኲሎ ነገረ ፍጥረት፤ » ነው። ኲፋሌ ፪፥፬። በተጨማሪም የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመልከት።

-       « ኢትኅፈር ነገረ ጌጋይከ የኃጢአትህን ነገር መናገር አትፈር » ሢራ ፳፮
-       « መኑ ይክል ነጊረ ምሕረቱ ጥንቁቀ የምሕረቱን ነገር ጠንቅቆ መናገር የሚቻለው ማነው ? » ሢራ ፲፭
-       « ዘአቅደመ ነጊረ በአፈ ነቢያት በነቢያት አፍ አስቀድሞ ያናገረው » ሮሜ ፥፪
-       « ለምንት ትነግር ሕግየ፤ ለምን አንተ ሕጌን ትናገራለህ ? » መዝ ፵፱ ፲፭
-       « ፈሪህየ ከመ እንግርክሙ ዘእኄሊ ዕውቀቴን የማስበውን እነግራችሁ ዘንድ ፈርቼ ዝም አልሁ » ኢዮ ፴፪
፩፥፪ - ቅዱስ ማለት በቁም ሲተረጐም የተቀደሰ ክቡር ምስጉን ልዩ ምርጥ ንጹሕ ጽሩይ ማለት ነው። ለብዙ ሲሆን ቅዱሳን ይባላል። በአጠቃላይ « ነገረ ቅዱሳን » የሚለው ሲተረጐም፦  የቅዱሳንን ነገር መናገር መስበክ ማስተማር ማብሠር መጻፍ ይሆናል።
፪፡- ቅዱስ ማነው?
          ከሁሉ በላይ ቅዱስ የሚባለው እግዚአብሔር ነው። ጥንትም ዛሬም ለዘላለምም (ቅድመ ዓለም ማዕከለ ዓለም ድኅረ ዓለም) ቅዱስ ነው። በቅድስናም የሚመስለው ማለትም የሚተካከለው  የለም፡፡ ነቢዩ አሳይያስ « እንግዲህ እተካከለው  ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ » በማለት የነገረን ይኽንን ነው ኢሳ ፳፭ ፡፡

፪፥፩ ስሙ ቅዱስ ነው
          የእግዚአብሔር ስም ፍጡራን ከሚጠሩበት ስሞች ሁሉ የተለየ ነው። ባሕርዩን ግብሩን የሚገልጥ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ « ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስም » ያለው ለዚህ ነው። « ወተወከልነ በስሙ ቅዱስ በቅዱስ ስሙ ታምነናልና » እንዲል ይህ ስም መታመኛ ነው። መዝ ፴፪ ፳፩ ጠላቶቻችንን የምንወጋው በላያችን ላይ የቆሙትን የምናዋርደው በስሙ ነው። መዝ ፵፫ ፥፭። ቅዱስ ዳዊት፡- ንብ ማርን እንደሚከብ የከበቡትን አሕዛብ ያሸነፋቸው በእሳት እንደተያያዘ ደረቅ የእሾህ ክምር ያነደዳቸው ቅዱስ በሆነው በእግዚአብሔር ስም ነው። መዝ ፩፻፲፯ ፥፲። በጐልያድ ፊት በቆመ ጊዜም « አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።» ብሎታል። በጦር ተወግቶ በሰይፍ ተመትቶ በፈረስ በሰረገላ ተገፍትሮ የማይወድቀውን ጐልያድን በእግዚአብሔር ስም በጠጠር ጥሎታል። ፩ኛ ሳሙ ፲፯ ፵፭
          በአዲስ ኪዳንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስሙ አጋንንትን እንደሚያወጡ ለደቀመዛሙርቱ ተናግሮላቸዋል። ማር ፲፮ ፥፲፯ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ በቤተ መቅደስ ደጅ ያገኙትን አንካስ በስሙ አርትተውታል። የሐዋ ፥፮ አይሁድ በተደነቁ ጊዜም « በስሙም በማመን ይህንን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው » በማለት መስክረውላቸዋል። የሐዋ ፫፥፲፮ በኢዮጴ ጣቢታ ከሞት ልትነሣ የቻለችው ቅዱስ ጴጥሮስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለቀሰቀሳት ነው። የሐዋ ፱፥፴። « ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና » በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰከረለት ቅዱስ ጳውሎስም ጠንቋዩን በርያሱስን በጌታ ስም ጨለማ አልብሶታል። የሐዋ ፲፫ ፥፲። የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባትንም ሴት ፈውሷታል። የሐዋ ፲፮ ፥፲፮
፪፥፪ ባሕርዩ ቅዱስ ነው
          የእግዚአብሔር ባሕርይ ልዩ ነው። የባሕርይ መገለጫዎቹም ብዙ ናቸው። እግዚአብሔር ፈጣሪ ፥ጌታ አምላክ ንጉሥ ነው ሁሉን የያዘ ሁሉን የጨበጠ ነው፤ ሁሉን የጀመረ ሁሉን የጨረሰ ነው ከዓለም አስቀድሞ የነበረ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዘለዓለማዊ ነው፤ የሚሳነው የሌለ ሁሉን ቻይ ነው ምሉዕ በኲላሄ ነው ዐዋቂ ጥበበኛ ሕያው ኃያል ረቂቅ መሐሪና ቅዱስ ነው ፈታሒ በጽድቅ ኰናኒ በርትዕ ነው መፍቀሬ ሰብእ ነው መዓቱ የራቀ ምሕረቱ የበዛ ትእግሥተኛ ነው መምህር ብርሃን አዳኝ መጋቢ ጠባቂ ረዳት ባዕለጸጋና አባት ነው።
          ቅዱሳን መላእክት የባህርዩን ቅዱስነት አውቀው፦ « ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች » እያሉ በአንድነት በሦስትነት ያመሰግኑታል። ኢሳ ፥፫። እሥራኤል ዘሥጋ ከባርነት ቤት የታደጋቸውን እግዚአብሔርን « አቤቱ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማነው? በምሥጋና የተፈራህ ድንቅንም የምታደርግ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማነው » እያሉ ዘምረውለታል። ዘጸ ፲፭ ፲፮። ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን « የእስራኤል ቅዱስ » ብሎታል። ኢሳ ፲፮ ፵፯ ፬። በአጸደ ነፍስ ያሉ ሰማዕታትም፦ « ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከመቼ አትበቀልም። » ሲሉ ተሰምተዋል ራእ ፮፥፱-፲፩

No comments:

Post a Comment